ዶክተር ደሳለኝ ሞላ የወልድያ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ

81
ወልድያ ሰኔ 30/2010 ለወልድያ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንትነት በተካሄደ ውድድር ዶክተር ደሳለኝ ሞላ አሸናፊ ሆነው መመረጣቸውን ዩኒቨርስቲው አስታወቀ። የዩኒቨርስቲው የህዝብና የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ከበደ ዛሬ እንዳስታወቁት አዲስ የተመረጡት ፕሬዚዳንቱ ለቀጣይ ስድስት ዓመታት ዩኒቨርስቲውን በበላይነት ይመራሉ። ዶክተር ደሳለኝ በትምህርት ዝግጅት፣ በአመራርና የሥራ ልምዳቸው፣ በስትራቴጂክ እቅድ ይዘትና አቀራረብ እንዲሁም በሌሎች ውድድሮች አሸናፊ መሆናቸውን ተናግረዋል። የተወዳዳሪዎች ውጤት ትናንት ለዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ይፋ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ በውድድሩ አሸናፊ የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ሞላ የውድድር ውጤታቸው ለትምህርት ሚኒስቴር መላኩንም ተናግረዋል፡፡ ዶክተር ደሳለኝ በበኩላቸው በመጭዎቹ ዓመታት በዩኒቨርስቲው ወቅቱ የሚጠይቀውን የአካዳሚክ ነፃነትን ለማስፈንና ያልተማከለ አሰራርን ለመከተል እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ የገለፁት ዶክተር ደሳለኝ የሠራተኛውን አቅም ለማሳደግ እንደሚሰሩም ገልፀዋል። የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢና በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አበራ ሰይፉ በበኩላቸው ካለፈው የካቲት ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ እጩዎችን በመመልመል ኮሚቴው ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀዋል። ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀ ዩኒቨርስቲውን ላለፉት ሰባት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት መምራታቸው ይታወሳል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም