የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ስፖርታዊ ውድድሩ ሁሉ በምርምር ስራዎችም እንዲተባበሩ ተጠየቀ

1464

መቀሌ ሰኔ 30/2010 የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች በስፖርታዊ ውድድር የጀመሩትን ግንኙነት በምርምር ስራዎችም ሊያጠናክሩት እንደሚገባ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ለአንድ ሳምንት ሲካሔድ የቆየው ዘጠነኛው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርታዊ ውድድር በኡንጋንዳ ዩኒቨርሲቲዎች አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ትላንት ማምሻውን በተከናወነው የውድድሩ ማጠናቀቂያ ስነ-ስርዓት ላይ እንደተናገሩት የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያካሒዱት ስፖርታዊ ውድድር ከፍ ያለ መቀራረብን የሚፈጥር ነው።

ዩኒቨርሲቲዎቹ በስፖርታዊ ውድድሩ ከሚያደርጉት ግንኙነት ባለፈ እንደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምነታቸው በምርምር ስራዎችም አብረው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ማሉምቤት ራሌዝ በበኩላቸው ዝግጅቱ “አፍሪካዊነታችንን ያቀራረበና በቀጣይ ውድድሮችም ይበልጥ እየተቀራረብን እንድንሄድ ያስቻለ ውድድር ነበር” ብለዋል።

የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤልም በተመሳሳይ፣ “አፍሪካዊያን ወጣቶች የአህጉሪቷ ተረካቢዎችና ተስፋ በመሆናቸው በስፖርታዊ ውድድሩ ወዳጅነታቸውንና አንድነታቸውን ይበልጥ  ሊያጎለብቱበት ይገባል” ብለዋል።

በዘጠነኛው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ስፖርታዊ ውድድር ላይ በአጠቃላይ ውጤት የኡጋንዳ ዩኒቨርሲቲዎች ቡድን በ16 የወርቅ፣በ17 የብርና በ11 የነሃስ ሜዳሊያዎች አንደኛ በመሆን አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች በ15 የወርቅ፣ በ20 የነሓስና በ22 የብር ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ በ12 የወርቅ፣በሶስት የብርና በሶስት ነሐስ ሜዳሊያ ደግሞ የጋና ዩኒቨርሲቲዎች ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።

በውድድሩ ላይ ከ16 የአፍሪካ ሀገራት የተወከሉ 56 ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ 900 የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች ተሳታፊ ነበሩ።

ለአንድ ሳምንት በተካሄደው አጠቃላይ ውድድር በወንዶች የጋና ዩኒቨርሲቲዎች በሴቶች ደግሞ የኡጋንዳ ዩኒቨርሲቲዎች አሸናፊዎች ሆነዋል።