አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ስራ እንዲሰማሩ የመረጃ ትስስር ይፈጥራል

67
አዲስ አበባ ሰኔ 30/10/2010 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያስመርቃቸው ተማሪዎች ወደ ስራ እንዲሰማሩ የሚያስችል የመረጃ ትስስር ከመንግስታዊና ከግል ድርጅቶች ጋር ለመፍጠር እንደሚሰራ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 9ሺህ724 ተማሪዎች ዛሬ በሚሌኒየም አዳራሽ አስመርቋል። በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ወቅት ፕሬዚዳንቱ ፕሮፌሰር ጣሰው እንደተናገሩት፤ ተመራቂዎች የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው የሚያስችል ትስስር ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ትስስር ለመፍጠር ይሰራል። ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ተልዕኮውን ለመወጣት ከመቼውም በላይ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ከመማር ማስተማሩ ጋር በተያያዘ ዩኒቨርሲቲው ከተያዘው አመት ጀምሮ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተግባር የታገዘ ትምህርትና የህይወት ዘመን ክህሎት ለመስጠት በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ተመራቂዎች ወደ ስራ ሲሰማሩም አስፈላጊውን ክህሎትና እውቀትን እንዲያገኙ  ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራልም ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሚካሄዱ የምርምር ስራዎች የአገሪቱን ፍላጎት  መሰረት ያደረጉ ናቸው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ይህንንም እውን ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ከየኢንዱስትሪዎች ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ በዚህም 2010ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከ200 በላይ የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ህብረተሰቡ ማሰራጨታቸውንም ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ከአንድ ሺህ በላይ የምርምር ህትመቶችን በአገርና በአለም አቀፍ ደረጃ በሚገኙ ጆርናሎች ላይ ማሳተም መቻሉን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡ በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍም ዩኒቨርስቲው ከአገር አልፎ ለአፍሪካ አገሮችም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በዚሁ ዘርፍ ዩኒቨርስቲው በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 80 ሚሊዮንብር የሚገመት የነጻ ህክምና ለህሙማን እንደሰጠ ተናግረዋል። እንዲሁም ሰኔ 16 በሀገሪቱ እየመጣ ያለውን ለውጥ ለመደገፍ በመስቀል አደባባይ በወጡ ንጹሀን ላይ በተወረወረ ቦንብ ለተጎዱ ዜጎች ህክምና ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ምርምሮችን በማከናወኑ በኢትዮጵያ ብቸኛው የምርምር ዩኒቨርሲቲ በመሆን የአፍሪካ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ማህበር ለመሆን መብቃቱንም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው በሚሰራቸው ስራዎች ምክንያት ከኢትዮጵያ አንደኛ፣ ከምስራቅ አፍሪካ ሁለተኛ፣ ከመላው አፍሪካ 16ኛ  እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ 1003ኛ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንቱ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው በቅድመ ምረቃ 32 ሺህ 230፣ በድህረ ምረቃ 17 ሺህ 818 ተማሪዎችን በአጠቃላይ 50 ሺህ ተማሪዎችን በ73 የቅድመ ምረቃ፣ በ344 የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች እያስተማረ ይገኛል። ከዚህም ውስጥ ከ200 በላይ ተማሪዎች የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ፣ ከ450 በላይ የሚሆኑትም አካል ጉዳተኞች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም