በኢትዮጵያ ተጨማሪ 169 ሰዎች ኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው ሲሆን የአንድ ሰው ህይወት አልፏል

80

ግንቦት 28/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት በተደረገ 5798 የላቦራቶሪ ምርመራ ተጨማሪ 169 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸውና የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

በዚህም በሀገሪቱ እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች 1805 ደርሷል።።

ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የተረጋገጠ ሰዎች ከ 1 እስከ 78 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ 111 ወንድና 58 ሴት ሲሆኑ፤ 168 ኢትዮጵያውያንና አንድ አሜሪካዊ ዜግነት ያለው መሆኑ ታውቋል።

ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 138 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 4 ሰዎች ከትግራይ፣ 4 ሰዎች ከደቡብ ብሔርብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ 11 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 6 ሰዎች ከአማራ ክልል፣ 1 ሰው ከሐረሪ ክልልና 5 ሰዎች ከሶማሌ ክልል መሆናቸው ተገልጿል።

በቫይረሱ አንድ የ35 አመት ሴት ኢትዮጵያዊ ሕይወት ያለፈ ሲሆን እስካሁን የ 19 ሰዎች ህይወት አልፏል።

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በህልፈተ ህይወቱ የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቹ መጽናናትን ተመኝተዋል።

በሌላ በኩል ትላንት ከአማራና ከቤኒሻንጉል ክልል 12 ሰዎች(10 ከአማራ ክልል፣ 2 ከቤኒሻንጉል) ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች 262 ናቸው።

በአጠቃላይ ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በለይቶ ህክምና ውስጥ ያሉ 1522 ሰዎች ሲሆኑ ከነዚህ መካከል 18ቱ በፀና የታመሙ መሆናቸውን ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።

የላቦራቶሪ ምርመራ ናሙናዎች ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ተወስዶ የተከናወኑ መሆኑም ተገልጿል።

እስካሁን አጠቃላይ 131, 368 የላቦራቶሪ ምርመራ ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም