አንድ አትሌት ከማናቸውም ውድድሮች እገዳ ሲጣልበት የሁለት አትሌቶች ጉዳይ እየተጣራ ነው

464

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28/2012 (ኢዜአ) አትሌት ወንድወሰን ከተማ አበረታች መድኃኒት በመጠቀሙ የአራት ዓመት እግድ ተጣለበት። 

የሁለት አትሌቶች ጉዳያቸው በመጣራት ላይ መሆኑንም ብሔራዊ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

ጽ/ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አትሌት ወንድወሰን ከተማ ማሞ እ.አ.አ ታኅሣሥ 1/2019 በቻይና ሻንዚቢ ዓለም አቀፍ የግል ማራቶን ውድድር ላይ በስፖርት የተከለከለ አበረታች መድኃት (ዶፒንግ) መጠቀሙ በመረጋገጡ ለአራት ዓመታት የእግድ ቅጣት ተጥሎበታል ብሏል።

አትሌቱ በማንኛውም አገር አቀፍ ይሁን ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፍ ነው ቅጣቱ የተጣለበት።

በዚህ ውድድር ላይ ብቻ ያስመዘገበው ውጤትና ሽልማት እንዲሰረዝ ዉሳኔ መተላለፉን የፀረ አበረታች ቅመሞች ጽ/ቤት አስታውቋል።

ብሔራዊ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት በመግለጫው አትሌቱ በግል በተሳተፈበት ውድድር ላይ ካዚኖኔ የተባለውን አበረታች  መድኒት መጠቀሙ በመረጋገጡ ነው እገዳው የተጣለበት።

በተጨማሪም ሁለት አትሌቶች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በግላቸው በተሳተፉባቸው ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን መጠቀማቸው ጥርጣሬ በመኖሩ ጉዳያቸው በመጣራት ላይ መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።

የሁለቱ አትሌቶች ዉሳኔው እንደተጠናቀቀም ቅጣቱንና ሥም ዝርዝራቸው የሚያሳውቅ መሆኑን ገልጿል።

ከኮረና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ስፖርታዊ ውድድሮች ለጊዜው ቢቋረጥም የስፖርት አበረታች ቅመሞች ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጽ/ቤቱ አመልክቷል።

በተለያየ መልኩ የሕግ ጥሰት በሚፈጽሙ አትሌቶች ጀርባ ሆነው ተሳታፊ በሚሆኑ ግለሰቦች ላይ የእርምት እርምጃ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆነኑን ጨምሮ አስታውቋል።

ስፖርተኞችም ራሳቸውን ከኮረና ወረርሽኝና ከስፖርት አበረታች ቅመሞች እንዲጠብቁ ጽሕፈት ቤቱ ጥሪ አድርጓል።