የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የርብርብ ማዕከል ሊሆን ይገባል… ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

74

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2012( ኢዜአ) የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የኅብረተሰቡ የርብርብ ማዕከል ሊሆን እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

ኢትዮጵያ በ 2011 ዓመተ ምህረት በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አራት ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ችላ ነበር።

በዚሁ ዓመት በሐምሌ 22 ደግሞ በአንድ ጀምበር ከ350 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል የዓለም ክብረ ወሰን (ሪከርድ) መስበሯም ይታወቃል።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዛሬ ከመከላከያ ሠራዊት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በተደረገው ድጋፍ ላይ እንደተናገሩት በተያዘው ዓመት አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዟል።

በዚህም ካለፈው ዓመት የተገኙ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን እንደልምድ በመውሰድ ዘንድሮ በተሻለ ቁመናና ሳይንሳዊ ዘዴ ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘንድሮው ዓመት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዛሬ እንደተጀመረ ገልጸው፤ “ኅብረተሰቡ አረንጓዴ አሻራ የልማታችንና የሌጋሲያችን አካል ማድረግ አለበት” ብለዋል።

ኅብረተሰቡ ከዛሬ ጀምሮ ኮቪድ-19ን ከመከላከል ጎን ለጎን ችግኝ ተከላና እንክብካቤን የርብርቡ ማዕከል እንዲያደርግ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የደን ሽፋኗን 30 በመቶ ለማድረስ እየሰራች መሆኑን የአካባቢ ደን የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን መረጃ ያሳያል።