ባንኩ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት በሚል አዲስ ስያሜና መለያ መጀመሩን አስታወቀ

194

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱን በአዲስ ስያሜና መለያ መጀመሩን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ገለጹ።

አገልግሎቱን ሲ ቢ ኢ ኑር ብሎታል።

ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት በቅዱስ ቁርዓን ያልተፈቀዱ የንግድ ዘርፎችን አለመስራትና አለመደገፍን ያካትታል። ለአብነትም የአሳማና የአልኮል ንግድና የመሳሰሉትን ሽያጭን ያካትታል።

አገልግሎቱ በዓለም ላይ እያደጉ ከመጡ የአገልግሎት ዘርፎች ተጠቃሽ መሆን እየቻለ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት ባንኩ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎትን  ለማስፋፋት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

ባንኩ ከሰባት ዓመታት በፊት በ22 ቅርንጫፎች መጀመሩን አስታውሰው፤አሁን ከ53 በላይ ቅርንጫፎች አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በአገልግሎቱ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚደርሱ ደንበኞችን ያፈራ ሲሆን፤ከ30 ቢሊዮን በላይ ብርም ተቀማጭ ሆኗል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

በአገልግሎቱ የሚጠቀሙት እምነታቸው የማይፈቅድላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ሲሆኑ፤አገልግሎቱ ገንዘባቸውን ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ለማስቀመጥና ከሌሎች ጋር ተጋርተው ለመሥራት እንደሚያስችላቸው አቶ አቤ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል።