ግድቡን የምንገነባው እንደ ሃውልት አቁመን ልናየው አይደለም ... አቶ ንጉሱ ጥላሁን

141

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2012(ኢዜአ) ''ግድቡን የምንገነባው እንደማንኛውም ሃውልት አቁመን ልናየው አይደለም'' ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ።

አቶ ንጉሱ ይህን ያሉት ዛሬ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የዜና አውታር ከሆነው አል-አይን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።

በዚሁ ጊዜ ''ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን የጀመረችው ማንንም የውጭ ሃይል ተማምና አይደለም'' ብለዋል።

ግድቡ የአገሪቷን የልማት ጥያቄ ከመመለስ ውጪ የትኛውንም አገር የመጉዳት ዓላማ እንደሌለው በተደጋጋሚ ማሳወቋንም ጠቅሰዋል።

''ግድቡን እየገነባነው ያለነው እንደማንኛውም ሃውልት አቁመን ልናየው ሳይሆን የዜጎችን የመልማት ጥያቄ ልንመልስበት ነው'' ሲሉ ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ የሌሎችን ጥቅም ሳትነካ በራሷ አቅም የተፈጥሮ ሃብቷን በማልማት እንዳትጠቀም የትኛውም አካል ሊከለክላት እንደማይችል ያስገነዘቡት አቶ ንጉሱ፤ የውሃ ሙሌት ስራው በታቀደው መሰረት እንደሚከናወንም አረጋግጠዋል።

ግድቡ ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው ጥቅም ባልተናነሰ መልኩ ለሱዳናውያን የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።  

የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአሁን ጊዜ 73 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም