ኢትዮጵያና ሱዳን ይህ ነው የሚባል የጥቅም ግጭት የላቸውም -- አቶ ንጉሱ ጥላሁን

136

አዲስ አበባ ግንቦት 27/2012(ኢዜአ) ኢትዮጰያና ሱዳን ይህ ነው የተባለ የጥቅም ግጭት እንደሌላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ። 

ድብቅ አጀንዳ ያላቸው የመገናኛ ብዙሃን ሰሞኑን በኢትዮ-ሱዳን ድንበር አካባቢ ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት በተሳሳተ መልኩ ማቅረባቸውንም ተናግረዋል።

አቶ ንጉሱ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የዜና አውታር ለሆነው አል አይን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያና ሱዳን የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ከመሆናቸው ባለፈ ረጅም ድንበርም ይጋራሉ ብለዋል።

ይሁንና የአገራቱ ድንበር ወጥ በሆነ መንገድ አለመካለሉ የትኛውም አካባቢ እንደሚያጋጥመው አልፎ አልፎ የሚነሱ ግጭቶች ይኖራሉ ብለዋል።

ይህ በአካባቢው ነዋሪዎችና አስተዳደር መፍትሄ እያገኘ እንደሚሄድም ተናግረዋል።

ይሁንና ድብቅ አጀንዳ ያላቸው መገናኛ ብዙሃን ሰሞኑን በኢትዮ-ሱዳን ድንበር አካባቢ የተፈጠረውን ችግር በተሳሳተ ሁኔታ በማቅረብ የሁለቱን ወንድማማች ሕዝቦች ግንኙነት ለማጠልሸት ያደረጉት ሙከራ አለመሳካቱን ነው የገለጹት።

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያና ሱዳን ይህ ነው የሚባል የጥቅም ግጭት እንደሌላቸው ያሳያል ብለዋል።

"ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላት ግንኙነት በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ነው" ያሉት አቶ ንጉሱ ክብርና ጥቅሟን በመዳፈር በሉዓላዊነቷ ላይ የሚመጣን በሃይል መመከትን ተክናበታለችም ብለዋል።

እንደ አቶ ንጉሱ ገለጻ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የተጋነነና ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ በማቅረብ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የቆየ ወዳጅነት ለማደፍረስ ጥረት ያደርጋሉ።

ሰሞኑን የተፈጠረው ግጭት ከወትሮው የተለየ ነገር ባይኖረውም መገናኛ ብዙሃኑ የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማውጣት ተጠቅመውበታል።

መረጃው ለኢትዮጵያ፣ ለሱዳንም ሆነ ለግብጽ ሕዝብ የማይጠቅም በመሆኑ ህብረተሰቡ መረጃዎቹን ከትክክለኛ ምንጭ እንዲያጣራ ጠይቀዋል።

የሱዳንም ሆኑ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጭምር በመግባት በሕዳሴ ግድቡም ሆነ በድንበር አካባቢ ያለውን ትክክለኛ መረጃ በተሳሳተ መልኩ የማቅረብ አዝማሚያ እንዳላቸው አቶ ንጉሱ ጠቁመዋል።

የሱዳን ሕዝብ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ታሪካዊና ባሕላዊ ትስስር ግምት ውስጥ በማስገባት ለተሳሳቱ መረጃዎች ጆሮውን እንዳይሰጥም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ያላቸውን ትስስር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን በአዲስ አበባ መምከራቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም