ከባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ በ9 ወራት ውስጥ 19 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱ ተገለጸ

134

አዲስ አበባ ግንቦት 27/2012(ኢዜአ) በ2012  በጀት አመት 9 ወራት ውስጥ ከአጠቃላይ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ 19 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ። 

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት የአገሪቱን የገቢና ወጪ እቃዎች በተለያዩ አገሮች በማጓጓዝ ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይታመናል። 

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሮባ መገርሳ፤ በ2011 ዓ.ም በጀት አመት 9 ወራት ውስጥ ብቻ 9 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቶን ጭነት ወደ አገር ውስጥ ማስገባት መቻሉን አስታውሰዋል።

በ2012 በጀት አመት 9 ወራት ውስጥም ነዳጅን ጨምሮ 12 ሚሊዮን ቶን ጭነት መግባቱን ገልጸው፤ ''ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ37 በመቶ ጭማሪ አለው'' ብለዋል።

በዚህም በዘርፉ በአጠቃላይ 19 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ መከሰት ከፍተኛ ተጽእኖ ካሳደረባቸው ዘርፎች መካከል የባህር ትራንስፖርት ዘርፉ አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህም ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ዘርፉ 75 በመቶ ኪሳራ እንዳጋጠመው ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱት የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች የወረርሽኙ ተጋላጭ እንዳይሆኑና ችግሩ ቢከሰትም የህክምና እና ሌሎች አገልግሎቶችን ሊያገኙ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ በጂቡቲ ካሉ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተለይም ድንበር ላይ የህክምና ማዕከል የማቋቋምና አሽከርካሪዎች ተጋላጭ የሚሆኑበት ሁኔታ ሲፈጠርም የሚቆዩበት ቦታዎችን የማዘጋጀት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ተናግረዋል።

ተቋሙ በኪቪድ-19 ምክንያት የተጎዳውን ዘርፍ እንዲያገግም ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመረከ እንደሚገኝም አቶ ሮባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም