ኮቪድ-19ኝ እና የአመራሩ ምላሽ በኢትዮጵያ

147

ይርጋ ምትኩ (ኢዜአ)

በሀገራችን የመጀመሪያው በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው ሪፖርት ከተደረገ በኋላ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማውጣት ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል። ማህበራዊ የሆኑ ጉዳዮችን ካነሳን የጤና የምርመራ ጣቢያዎችን ከማጠናከር እስከ ማዕድን ማጋራት ተግባራትን የመምራት ሚናው ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀስ ነው።

በተለይ የዜጎች የእርስ በርስ መረዳዳት ባህል እንዲዳብር በማድረግ ያለው ለሌለው እንዲያካፍል የተደረገበት አግባብ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ እናገኘዋለን።

በምጣኔ ሃብቱ ረገድም የተወሰዱ ጉልህ እርምጃዎችን መጥቀስ ቀላል ነው።  በተለይ ለፋይናንስ ተቋማት፣ ለሆቴሎች እንዲሁም ለሌሎች ተቋማት የተደረጉ የመታደጊያ ድጋፎች መንግስት ለችግሩ መላ በመፈለጉ ሂደት ጠንካራ ስራ መስራቱን ያሳያል። መንግስትና ህዝብ እስካሁን ውጤታማ ሆነው እየከወኑት ስላለው ተግባር በርካታ ምስክርነቶች እየተሰጡ ይገኛል። ከነዚህም ውስጥ ODI የተሰኘው ድረ ገፅ ይዞት የወጣው አንዱ ነው።

overseas Development Institute በምህፃረ ቃሉ ODI አለም አቀፍ የቲንክ ታንክ ዌብ ሳይት ነው። በዚህ ዌብ ሳይት ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች እየተስተናገዱ ሃሳቦች ይንሸራሸሩበታል። ሰሞኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ በዚህ ዌብ ሳይት ላይ ‘Adaptive leadership in the Covid-19 response: insights from Ethiopia’ በሚል ርዕስ ፅሁፍ አስፍረዋል።   

በአንድ ሀገር ላይ የሚከሰቱ ስጋቶችን በተለይም እንደ ኮሮና ቫይረስ ያሉ አለም አቀፍ ወረርሽኝ በሰው ልጆችና በሀገር ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ወሳኙ መሳሪያ የአመራርነት ጥበብ ነው ይላሉ ጽሑፋቸውን ሲጀምሩ ዶክተር አርከበ፡፡

በተለይም የኅብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረቶች በሚናወጡበት ጊዜ መሪዎቹ ለየት ያለ አመራር መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሆነ ሆኖ በቂ ያልሆነ ማስረጃ ፣ ያልተሟላ ሳይንሳዊ ምክር እና አለመተማመን በሚፈጠርበት ጊዜ ፈጣን እና ደፋር ውሳኔዎች መወሰድ አለባቸው፡፡ ለዚህም የአስፈጻሚ አካላት አመራር ሰጪነት ወሳኙን ስፍራ ይይዛል፡፡

መንግስት የኮሮና ወረርሽኝ ሊያደርስ የሚችለውን ሁለንተናዊ ቀውስ ለመቀነስ የወሰዳቸው እርምጃዎች የሚበረታቱ ናቸው፡፡ እንደ አብነትም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንደ ማቆያ ማዕከላት መጠቀምን ጨምሮ ወደ 11 ሚሊዮን የሚጠጉ አባወራዎችን የቤት ለቤት ምርመራ ማድረግ መቻሉ መንግስት ለወረርሽኙ የሰጠውን ልዩ ትኩረት አመላካች መሆናቸውን በጽሑፋቸው ያነሱታል፡፡

አያይዘውም ዶክተር አርከበ  በተለይም ብዙዎቹ ሀገራት እየወሰዱት ያለውን ቤት የመቆየት ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ የህዝቡን ተጨባጭ የኑሮ ደረጃ ታሳቢ ያደረጉ እርምጃዎችን መውሰዷ ተገቢ ነው ፡፡እነዚህን እርምጃዎች እንደ ህገ ወጥነት የሚቆጥሩ አካላት ሊኖሩ ይችላሉ  ሆኖም ግን መንግስት  የመጀመሪያው የቫይረሱ ተተኪ ሪፖርት ከተደረገበት መጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ የተቀናጁ አገራዊ ምላሾችን ለመስጠት መስራቱ ተገቢነት ያለው መሆኑን ያትታሉ በጽሑፋቸው፡፡

መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃም በአብዛኛው አዎንታዊ ውጤቶችን እያሳየ ያለበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ ያቀረቡት በአገሪቱ የመጀመሪያው የቫይረሱ ተተኪ ከተገኘበት ቀን ጀምሮ እስካሁን ያለው የቫይረሱ ስርጭት በአመዛኙ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑንና ውጤቱ በተለይም ከተመረመረው ህዝብ ብዛት ጋር ሲነጻጸር 0.5 ብቻ በቫይረሱ መለከፋቸውን ያሳያል ብለዋል በትንታኔያቸው፡፡

ሆኖም ቫይረሱ በአገሪቱ ቀጣይ ሊስፋፋ ስለሚችልና ወረርሽኙ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ አሁንም የመሪነት ስልት አብሮ ተስፈንጣሪ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ ለዚህም መንግስት የሚከተሉትን አራት አንኳር ነጥቦችን መሰረት በማድረግ ሊሰራ እንደሚገባ ምክራቸውን አስቀምጠዋል፡፡

1. ልዩ ሁኔታን መረዳት እና ያልተለመደ አካሄድ መከተል

በመጀመሪያ መንግስታት የኮቪድ -19 ወረርሺኝ ከየትኛውም ወረርሽኝና በሽታ በላይ የህብረተሰቡ የጤና ጠንቅ መሆኑን በመረዳት ትኩረት ሊያደርጉት ይገባል፡፡ ይህም ሲባል ወረርሽኙ ባልተጠበቀ ፍጥነት ሊዛመት ስለሚችል በዛው መጠን ሳይንሳዊ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ ዝግጅትና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ስኬታማነት አገራት ነባራዊ ሁኔታዎችን መሰረት ያደረጉ ስልታዊ እርምጃዎችን መውሰድ ግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያም ይህንን ታሳቢ በማድረግ ትኩረት ልታደርግ ይገባታል ብለዋል በጽሑፋቸው

2. ጥንካሬዎችን መቋቋም እና መገንባት

የኢትዮጵያ መንግስት አሁን ላይ የኮቪድ-19ኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተለይም በጠቅላይ ሚንስቴሩና በጤና ሚንስቴር በኩል የህዝቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚከውኗቸው የንቅናቄ ስራዎች ውጤታማና ወጪ ቆጣቢ ሆነዋል፡፡ በቀጣይም እነዚህን ከማጠናከር ጎን ለጎን በመከላከል ላይ የተመሰረተውን የጤና ስርዓትና ጤና   ኤክስቴሽንን ይበልጥ የማሳደግ ሥራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ምክራቸውን ለግስዋል፡፡

በተጨማሪም መንግስት ሕዝባዊ መሠረተ ልማቶችንና በመንግስት ባለቤትነት የተያዙ ድርጅቶች እንደ ባቡር ሀዲዶች እና የአየር ትራንስፖርት ያሉትን ጠንካራ ተቋማት ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ ከጥንካሬያቸው እንዳይወርዱ መስራትም አስፈላጊ መሆኑንም አያይዘው ገልጸዋል፡፡

3. ትብብር እና ሽርክና

ያለ ትብብር ስኬት ሊኖር አይችልም። የኢትዮጵያ መንግሥትም ከፌደራል ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ እያደረገ ያለው ቅንጅት እንዲሁም ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፡ ከሐይማኖት አባቶች፡ ከአገር ሽማግሌዎችና ከሌሎችም አካላት ጋር በሚያደርጋቸው ውይይቶችና ስምምነቶች ውጤት እያገኘ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በዘንድሮው ዓመት ሊካሄድ የነበረው ብሔራዊ ምርጫ ለሌላ ጊዜ መተላለፍ እንደቻለ በጽሑፋቸው አመላክተዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ ከተለያዩ ሀገር በቀልና የውጭ ሀገር ለጋሾችና የልማት አጋሮችን በማስተባበር የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለማሰባሰብና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች እንዲደርስ የሚደረገው ጥረት መጠናከር እንዳለበትና ይህም በወረርሽኙ ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በትንታኔያቸው ገልጸውታል፡፡ ይህም ችግሩን ለማለፍ ዋነኛ መሳሪ መሆኑንም ምክረ ሀሳብ አስቀምጠዋል፡፡

በተጨማሪም ለጋሾች እና ለልማት አጋሮች አቅርቦቶችን በማሰባሰብ እና  ተደራሽነት በመከታተል መንግስት ከኮቪድ -19 ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ጋር ተያያዥ መፍትሄዎችን ለማምጣት ከግሉ ዘርፍ ጋር እየተነጋገረ ይገኛል፡፡ ይህ በሁሉም ደረጃዎች ላይ የሚደረግ ትብብር የውጤቶች ቁልፍ አሽከርካሪ ይሆናል፡፡

4. መማር እና ማዳበር

ምንም እንኳን  ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሙሉ በሙሉ ቤት የመቀመጥ እርምጃ ተግባራዊ ባይደረግም  ህብረተሰቡ የተለያዩ ጥንቃቄዎችን እንዲያደርግ የወጡ ህጎችን የማጠናከር ስራ ያስፈልጋል፡፡ መንግስት ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ለሚያቀርቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ድጋፍና ክትትል በማድረግ የማበረታታት ስራ መስራት እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተለይም እንደ ሀገር ሊያጋጥሟት የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለመከላከልና ለመቀነስ አሁን ላይ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋሉ የመዘናጋት ተግባራትን ለማስቀረት ስራ እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል፡፡

ሀገሪቱ የምርመራ አቅምን ከማሳደግ ጀምሮ ህብረተሰቡ የፊት ጭምብል እንዲለብስ ፡ከአካላዊ ንክኪ እራሱን እንዲጠብቅ እስከ ማስገደድ የሚደርስ ስራ መስራት እንዳለባትና በድንበር አካባቢ የሚታየውን የላላ ቁጥጥር ማጠናከር ያስፈልገሳታል ሲሉም ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፤

ሌላው አገሪቱ ወረርሽኙ በኢኮኖሚያዊ ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ እና በተለይም በጣም የተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል ፡፡ ለኤክስፖርት ዘርፉም የታቀደውን ድጋፍን ማጠንከር አለበት ፡፡

መንግስት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህገ-መንግስቱን በማክበር እና በመጀመሪያ ዜጎችን ከወረርሽኙ መታደግ ዓላማ በማድረግ መስራት እንዳለባቸው በመጥቀስ ቀጣይ የሚደረገው ብሔራዊ ምርጫም ፍትሃዊና ነጻ ምርጫ የሚሆንበትን እድል የማመቻቸት ስራ መሰራት እንዳበትም አመላክተዋል፡፡

ዶክተር አርከበ ጽሑፋቸውን ሲያጠቃልሉ አሁን ላይ ባለው የወረርሽኙ ሁኔታ የኢትዮጵያንም ሆነ የሌሎች የአፍሪካ አገራትን የወደ ፊት እጣ ፋንታ መተንበይ አይቻልነም ሆኖም ግን እየታየ ያለውን ውጤት መሰረት በማድረግ ቀውሱ ሊያሻቅብ ስለሚችል ለዚህ ምላሽ የሚሰጥ የአመራር ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ ጽሑፋቸውን ደምድመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም