በአዳማ ከተማ 77 ሺህ 575 ብር ሐሰተኛ የብር ኖት ተያዘ

116

አዳማ ፣ግንቦት27/2012 (ኢዜአ) በአዳማ ከተማ 77 ሺህ 575 ብር ሐሰተኛ የብር ኖት ከአሳታሚዎቹ ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ ገለፀ ።

የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኝነት ባለሙያ ረዳት ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት አንዱ ግለሰብ ሐሰተኛ ኖት ይዞ ወደ ገበያ በወጣበት ወቅት ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ነው ።

ግንቦት 26 ቀን 2012 ዓ.ም  ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በአዳማ ከተማ ሉጎ ክፍለ ከተማ ቢቃ ቀበሌ ሁለተኛውና ዋነኛው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል ።

ፖሊስ ዋናው ተጠርጣሪ ተከራይቶ ከሚኖርበት አዱላላ ቀበሌ ሃጤ ሀሮሬቲ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ሐሰተኛ የብር ኖቶች ፣ ማተሚያ ማሽን ከነሙሉ እቃው ጋር በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉን ረዳት ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ተናግረዋል ።

በዚህም ባለ 100 ብር 75 ሺህ፣ ባለ 50 ብር 2 ሺህ 550 ብር፣ ባለ 10 ብር ሁለት፣ ባለ 5 ብር አንድ እንዲሁም የውጭ ሀገር ገንዘብ በቤቱ ውስጥ መገኘቱን ገልፀዋል ።

የሁለቱ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በምርመራ ላይ ሲሆን ምርመራው ሲጠናቀቅ ለፍርድ ይቀርባሉ ተብሏል ።

በተመሳሳይ ዜና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ በአንድ ቤት ውስጥ በአዳማ ከተማ ሉጎ ክፍለ ከተማ ጋረ ሉጎ ቀበሌ  ቀጠና 17 ተብሎ በሚጠራው ልዩ ቦታ 18 ሆነው ሲጠጡ የተገኙ ሰዎች መቀጣታቸውን ረዳት ኢንስፔክተሯ አያይዘው ገልፀዋል ።

የቤቱ ባለቤቶች የሆኑ ባልና ሚስት እያንዳንዳቸው 1 ሺህ 500 ብር የተቀጡ ሲሆን የተቀሩት 16 ሰዎች እያንዳንዳቸው 1 ሺህ ብር መቀጣታቸውን ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዳማ ከተማ ቦኩ ክፍለ ከተማ በሬቻ ቀበሌ በቀን ትናንት ከሌሊቱ 8 ሰዓት አካባቢ የአንድ ግለሰብ ንብረት  የሆኑ አራት ሱቆች መቃጠላቸውን ረዳት ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልጸዋል።

በእሳት አደጋው በአራቱ ሱቆች ውስጥ ያሉ ንብረቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን የገለፁት የህዝብ ግኑኝነት ባለሙያዋ፤ የአደጋው መንስኤ ኤሌክትሪክ መሆኑንም ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም