ድርጅቱ ኢትዮጵያ ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት አግዛለሁ አለ

56

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26/2012 (ኢዜአ) ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (I O M) ኢትዮጵያ ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ ገለጸ።

ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ሰዎችን እያጠቃና ሕይወት እየነጠቀ ይገኛል።

ቫይረሱ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱን ተከትሎም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትና ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

በተለይ የገንዘብና የቁሳቁስ  ድጋፍ በመንግሥታት፣ በውጭ በሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በባለሃብቶችና በሌሎችም የማህበረሰብ አባላት እየተደረገ ነው።

የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት በኢትዮጵያ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ዓለማየሁ ሰይፈ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ ከመንግሥትና ከሌሎችም ተቋማትና አካላት ጋር በመቀናጀት ወረርሽኙን በመከላከል እገዛ ነው።  

በተለይም በግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችና ተጓዦች በጉዞ ወቅት መደረግ በሚገባቸው ጥንቃቄዎች ላይ ስልጠናዎች፣ የሕክምና ባለሙያዎችና ቁሳቁስ እንዲሁም የምግብ አቅርቦት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ድጋፉንም በአዲስ አበባና በክልሎች እንደሚሰጥ ባለሙያው ተናግረዋል።

የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከገባ ጀምሮ እስካሁን 14ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ወደ አገራቸው ገብተዋል።

በዜጎቹ በለይቶ ማቆያ ጣቢያዎች ቆይተው እንደወጡ ገልጸው፤በአሁኑ ወቅትም 3ሺህ 500 የሚሆኑ ከስደት ተመላሾች በጣቢያዎቹ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ድርጅቱ በኮቪድ-19 ዙሪያ እርዳታ የሚሰጡ ከ390 በላይ የጽዳትና የጥበቃ ሠራተኞች እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም