በምዕራብ ወለጋ ዞን ከ156 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ ተዘጋጀ

122

ነቀምቴ፣ ግንቦት 26/2012 (ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ ዞን በመጪው ክረምት የሚተከል ከ156 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ በደሣ ኦልጅራ እንደገለፁት ችግኞቹ የሚተከሉት በዞኑ በ20 ወረዳዎችና በ3 የከተማ አስተዳደሮች ነው።

ለተከላ የተዘጋጁት ችግኞች በ2 ሺህ 422 የመንግሥት፣ የግል፣ የሃይማኖትና  ሌሎች ተቋማት የተዘጋጁ ናቸው።

ለተከላው 25 ሺህ ሔክታር መሬት የተለየ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ 82 ሚሊዮን ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውንም ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት ለተከላ ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል 20 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር ለመትከል የቦታ ልየታ ስራ ተከናውኗል።

እያንዳንዱ ነዋሪ 40 ችግኞችን እንዲተክል በተያዘው እቅድ መሰረት አፈፃፀሙን የሚከታተል ኮሚቴ ተቋቁሞ የቅድመ ተከላ ዝግጅት በማጠናከር ላይ ይገኛል ብለዋል።

ለተከላ የተዘጋጁት ችግኞች የፍራፍሬ ፣ የደን ዕጽዋትና የእንስሳት መኖርያዎች ያካተተ መሆኑን  አቶ በዳሣ ተናግረዋል።

ከዞኑ አርሶአደሮች መካከል የሀሩ ወረዳ የዱቺ ቀበሌ ነዋሪ ዋቅቶሌ ሞሲሳ በሰጡት አስተያየት በመጪው ክረምት 2 ሺህ 500 የጥድ ችግኞችን ለመትከል የጉድጓድ ዝግጅት ስራ እያካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዋቅጅራ ቀጠሌ በበኩላቸው የጥድ ችግኞችን ለመትከል የሚሆን መሬትና የሚተከልበት ጉድጓድ አዘጋጅቻለሁ ብለዋል።

በምዕራብ ወለጋ ዞን በ2011 ዓ.ም ከተተከሉት 20 ሚሊዮን  ችግኞች መካከል 73 በመቶ የሚሆነው መጽደቁን ከዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም