በኮቪድ 19 መከሰት ሳቢያ የደረቅ ወደቦች ገቢና ወጭ ንግድ መስተንግዶ 50 በመቶ ቀንሷል

46

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2012 (ኢዜአ) የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ደረቅ ወደቦች የሚያስተናግዱት የወጭና ገቢ ንግድ አገልግሎት 50 በመቶ ማሽቆልቆሉ ተገለፀ።

ከጅቡቲ ወጭና ገቢ ምርቶችን የሚያመላልሱ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎችን ከሚያስተናግዱ ደረቅ ወደቦች መካከል ከጅቡቲ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውና በ2002 ዓ.ም አገልግሎት የጀመረው የሰመራ ደረቅ ወደብና ተርሚናል አንዱ ነው።

የሰመራ ደረቅ ወደብና ትርሚናል ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቤኩማ ቲጫ ለኢዜአ እንዳሉት ወደቡ በሚሰጠው አገልግሎት ጅቡቲ ላይ የሚከፈለውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ረገድ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።

ቀደም ሲል ወደቡ በቀን እስከ 40 ወጭና ገቢ ዕቃዎችን የያዙ ኮንቴነሮችን ተቀብሎ የማራገፍ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።

አሁን ላይ ግን አልፎ አልፎ በቀን ከሚገቡ ከአንድ ወይም ሁለት ኮንቲነሮች በስተቀር በአብዛኛው ቀናት አንድም  ሳይቀበል እየዋሉ መሆኑን አቶ ቤኩማ ገልጸዋል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ የሰመራ ወደብና ተርሚናልን ጨምሮ በደረቅ ወደብ አገልግሎት አጠቃላይ አፈጻጽም በቀን ከ500 እስከ 600 ኮንቴነሮች ሲስተናገዱ ቆይተዋል።

አሁን ላይ ግን በቀን ከ100 እስከ 200 ኮንቴነሮች ብቻ እያስተናገዱ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ባለፈው አንድ ወር አጠቃላይ እንደ አገር የወደቦች የደረው ጭነት አገልግለት ክንውን አፈጻጽም 50 በመቶ ማሽቆልቆሉንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ካሏት ደረቅ ወደብና ተርሚናሎች መካከል ሰመራ፣ ድሬዳዋ፣ ሞጆ፣ ገላን፣ ቃሊቲ፣ ኮምቦልቻ፣ መቀሌና በቅርቡ የተገነባው የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናሎች ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም