በትግራይ ምእራባዊ ዞን በሳይንስና በቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራ 12 ተማሪዎችና መምህራን ሽልማት ተበረከተላቸው።

63

ሁመራ፣ ግንቦት 26/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ምዕራባዊ ዞን በሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ ውጤታማ የሆኑ 12 ተማሪዎችና መምህራን እውቅናና የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት ተበረከተላቸው።

ትናንት በተካሄደው የሽልማት ስነስርዓት ላይ የተገኙ በትግራይ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ የአህዝቦትና ትብብር ጊዚያዊ ዳይሪክተር አቶ ተክለመድህን ገብረስላሴ ለኢዜአ እንዳሉት በዘርፉ ውጤታማ ለሆኑ ሦስት መምህራንና 9 ተማሪዎች የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

 በዞኑ በርካታ የፈጠራ ስራ ያላቸው መምህራንና ተማሪዎች መኖራቸውን ያስታወሱት ጊዚያዊ ዳይሬክተሩ በዞኑ ለውድድር ከቀረቡ በርካታ የፈጠራ ስራዎች መካከል ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ብልጫ ያሳዩ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሸለሙ ተደርጓል ።

ተሸላሚዎቹ እንደየቅደም ተከተላቸው በነብስ ወከፍ ከአንድ ሺህ ብር እስከ ሁለት ሺህ 500 ብር ድረስ የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

 በውድድሩ አሸናፊ ሆነው ከተመረጡ የፈጠራ ሥራዎች መካከልም በኬሚካል፣ ኤሌክትሪካልና ማኒፋክቸሪንግ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ እንደሚገኙባቸው ተናግረዋል ።

የሽልማቱ ዋና ዓላማም በፈጠራ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦችን ይበልጥ እንዲበረታቱ መነሳሳትን ለመፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።

ከተሸላሚዎቹ መካከልም በዞኑ በጸገዴ ወረዳ ‘’የፍረቃልሲ’’ ትምህርት ቤት መምህር ሃይስላሴ አብርሃ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት በሦስት የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች ለውድድር ቀርበው በሦስቱም በአንደኝነት ማሸነፋቸውን ተናግረዋል።

ከፈጠራ ሥራዎቻቸው መካከልም አንዱ ″በኤስ ኤም ኤስ ″ሞባይል ተጠቅሞ ከርቀት የመስኖ ውሃ መሳቢያ ሞተር ማስነሳትን ፣ ሁለተኛው የፈጠራ ስራ ደግሞ በሪሞት ኮንትሮል ማናቸውም የተዘጉ በሮችና ለኮሮችን መክፈት የሚቻልበት ፈጠራ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም ሦስተኛ የፈጠራ ስራቸው ጥቅም ላይ ውለው የተጣሉ የተለያዩ የፕላስቲክ መያዣ ቁሶችን ተጠቅሞ እንደገና ለሌላ አገልግሎት እንዲውሉ ማስቻልን ይገኝበታል።

ከ2007 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ መድረኮች ፈጠራዎቻቸውን ለውድድር በማቅረብ ከክልል እስከ ሃገር አቀፍ ድረስ የነሃስ ሜዳሊያ ሽልማት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል።

የመካኒካልና ማኒፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የአካል ጉዳተኛ ዊልቸርና በአንድ ጊዜ እስከ አምስት ኪሎ ግራም ሲሚንቶ የማቡካት አቅም ያለው ማሽን ሰርቶ ጥቅም ላይ ያዋሉት መምህር ደረጀ ሐዱሽ በበኩላቸው ሁለተኛ ደረጃ በመውጣት ለሽልማት መብቃታቸውን ተናግረዋል።

የወዳደቁ ቁሶች እና ብረቶችን በማጠራቀም የሰሩት የፈጠራ ስራ እያንዳንዳቸው እስከ 15 ሺህ ብር ድረስ እየሸጡዋቸው እንደሆነም ነው ያስታወቁት።

የወተት ማቀነባበሪያ ማሽንና ከተለያዩ የፍራፍሬ ዘሮች ተስማሚ የፊት ቅባት የፈጠረችው የሁመራ ከተማ ነዋሪ ተማሪ ሊያ አደራጀው ደግሞ አንደኛ በመውጣት ተሸላሚ ሆናለች።

ለወደፊትም በቀላሉ የሚንቀሳቀስ የሲሚንቶ ማብኩያ /ሚክሰር/ ለመስራት እቅድ እንዳላት ተናግራለች።

የተበረከተላት የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማትም መነሳሳት እንድፈጠረላት ገልጻለች።

 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ጎን ለጎን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ለመበልጸግ መንግስት የቻለውን ያህል ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት የገለጹት ደግሞ በዞኑ ማህበራዊ ልማት የትምህርት ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ ዳንኤል መሰለ ናቸው::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም