በምእራብ ጎንደር የአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ማዕከላት በእጥፍ እንዲያድጉ ተደረገ

69

መተማ ፣ ግንቦት 26/2012 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ የሚገቡ ዜጎች ቁጥር በመጨመሩ የማቆያ ማዕከላት ቁጥር በእጥፍ እንዲያድግ መደረጉን የዞኑ ከሮና መከላከል ግብረ ሃይል አስታወቀ።

የግብረ-ኃይሉ አባል አቶ ብርሃኑ መንገሻ ለኢዜአ እንደገለፁት ዞኑ ከሱዳን ጋር ባለው ጉርብትና የኮሮና ወረርሽን እንዳይስፋፋ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ይገኛል።

በዚህም ከሱዳን የሚመጡ ዜጎችን በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ በማስገባት የመለየት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እስከ አሁን ስድሰት የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ተቋቁመው አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን ጠቅሰው በየጊዜው ድንበር አቋርጠው የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በመበራከቱ የማቆያ ማዕከላቱን ወደ 12 እንዲያድጉ ተደርጓል።

አዲሶቹ ማዕከላት ካለፈው እሁድ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልፀው ይህም በለይቶ ማቆያዎች የነበረውን መጨናነቅ በግማሽ መቀነስ እንደቻለ አስረድተዋል ።

በቀጣይም ተጨማሪ ሶስት የአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ቦታ ለማዘጋጀት የቦታ መረጣ እየተሰራ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

የማዕከላቱ መስፋፋት በአካላዊ መቀራረብ ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን የቫይረሱ መስፋፋት ለማስቀረት ያግዛል ብለዋል።

በየቀኑ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ከአንድ መቶ ያላነሱ ዜጎች ወደ ለይቶ ማቆያ ቦታዎች እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

በለይቶ ማቆያዎች ይስተዋል የነበረው የግብዓት አቅርቦትም በመንግስትና በአጋር ድርጅቶች የቁሳቁስ አቅርቦት በተወሰነ ደረጃ መፈታቱን ጠቅሰዋል።

በዞኑ በአሁን ወቅት ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች በለይቶ ማቆያ ማዕከላት ይገኛሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም