የፌደራልና የክልል የህግ አስከባሪ አካላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንብና የመመሪያ አፈፃፀምን ገመገሙ

50

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26/2012(ኢዜአ) የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከሕግ ማስከበር እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ከክልል የፍትህ አካላት አመራሮች ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ውይይት አካሂደዋል።

የኮሮና ቫይረስ ከሚያደርሰው ጉዳት ህዝባችንን ለመታደግ ክልሎች በቅንጅትና በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አሳስበዋል።

ዓቃቤ ህጓ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ ደንቦችን ለማስፈጸም የወጡ መመሪያዎች ተግባራዊና ተደራሽ ከማድረግ፣ ብሎም ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አንፃር የተግባራትን አፈፃፀም ግምገማ መነሻ ያደረገ ነው፡፡

የሕግ ጥናት ማርቀቅ እና ማስረጽ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በላይሁን ይርጋ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያ ቁጥር 3 እና 4 /2012 ዓ.ም ማሻሻያ የተደረገባቸውን እንቀጾች ያቀረቡ ሲሆን በግብይት ቦታዎች ዕቃን የሚሽጥ ማንኛውም ሰው አፍና አፍንጫውን መሽፈን፣ በሸማቹና በሻጩ መካከል ሁለት የአዋቂ እርምጃ ርቀት መጠበቅ የሚያስችል መገደቢያ የማዘጋጀት፣ እያንዳንዱን ሸማች በተናጠል ማስተናገድ አለባው ብለዋል።

እንዲሁም የሱቅ መደብሮችም ጭምር ንፅህናን ለመጠበቅ የሚያስችሉትን ውሃና ሳሙና ወይም ሳኒታይዘር ማዘጋጀት እንዳለባቸው ሕጉ እንደሚያስገድድ ገልጸዋል።

አቶ በላይሁን ይርጋ አክለውም የሀይማኖት አባቶችን ሳያካት ማንኛውም ሰው ከቤት ውጭ ማስክ ሳያደርግ መንቀሳቀስ፣ ከ6 ሰው በላይ ክርስትና ማስነሳት እና ከ20 በላይ ሆኖ የሰርግ ሥነ-ሥርዓት ማከናወን የተከለከለ መሆኑን በአዋጁ መካተቱን ተናግረዋል፡፡

የክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና የፖሊስ ተቋማት አመራሮች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎችንና አዋጁን በማስፈጸም ሂደት ውስጥ በጥንካሬ የተከናወኑ ተግባራትን፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ሪፖርት ቀርቧል፡፡

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ሕጎችን ለህዝብ እና ለሕግ አስከባሪዎች ግንዛቤ ለማስያዝ፣ ህብረተሰቡ አፍ፣ አፍንጫውን እንዲሸፍንና አለመጨባበጥ ላይ የተሰራው ስራ ጥሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም በግብይትና አገልግሎት መስጫ አካባቢዎች ከአተገባበር አኳያ ወጥነት አለመኖሩን ጠቁመው፣ ሕግን ስናስከብር ህዝቡ እየተገነዘበ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ዐቃቤ ህጓ አክለውም አገራዊ የኢኮኖሚም ሆነ የማህበራዊ እንቅስቃሴችን ሊቀጥል የሚችለው ወረርሽኙን ስንገታው በመሆኑ መዘናጋትን፣ ቸልተኝነትን እና መላመድን ማስቀረት አንደሚገባ አሳስበዋል።

ቀላል ወንጀል ፈጽመው በይቅርታ የተለቀቁ የሕግ ታራሚዎች ተመልሰው ወደ ጥፋት እንዳይገቡ ክትትል በማድረግ የሕግ የማስከበር ስራ በተጠናከረ መልኩ መስራት እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ከጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም