የአዲስ አበባ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ለጽዳት ሰራተኞች 40 ሺህ ማስክ ድጋፍ ሰጠ

89

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ በጽዳት ሥራ ለተሰማሩ አካላት 40 ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ድጋፍ አደረገ።
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ድጋፉ ለ15 ሺህ የመንገድ ጽዳት ፈጻሚዎች፣ ለህብረት ሽርክና ጽዳት ማህበራት እና በወረዳዎች ለሚገኙ የጽዳት አስተዳደር ባለሙያዎች የሚውል እንደሆነ ተገልጿል።

በጽዳት የተሰማሩት አካላትም ድጋፉን ከኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎች ተረክበዋል።

የአዲስ አበባ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ኃይማኖት ዘለቀ ”ድጋፉ የተደረገው ባለሙያዎቹ ራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ ጠብቀው ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ለማድረግ ነው” ብለዋል።

ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ ከሆኑ ዘርፎች መካከል አንዱ የጽዳት ዘርፍ እንደሆነ ተናግረው፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አገልግሎት እንዲሰጡ ከተለዩ የሥራ ዘርፎች መካከል እንደሚገኝበትም አመልክተዋል።

ሁሉም አካላት በጽዳት ሥራ ለተሰማሩ ሠራተኞችና ሙያተኞች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ወይዘሮ ኃይማኖት ጥሪ አቅርበዋል።

”የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመግታት ብሎም በከፍተኛ ሁኔታ እንዳይባባስ ለማድረግ የግልና የአካባቢ ፅዳትን መጠበቅ ወሳኝ ነው” ብለዋል።

ከዚህ በፊት በጽዳት ለተሰማሩት አካላት 24 ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ፣ 15 ሺህ ሊትር ሳኒታይዘርና አልኮል፣ እንዲሁም 7 ሺህ 500 ጥንድ ጓንት ድጋፍ መደረጉን ያስታወሱት ወይዘሮ ኃይማኖት፤ ተቋማትና በጎ አድራጊ ግለሰቦች  ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።