በቦሌ ክፍለ ከተማ 52 የኮንዶሚኒየም ሱቆች በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች ተሰጡ

138

የቦሌ ክፍለ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተረከባቸውን 52 የኮንዶሚኒየም ሱቆች በማህበር ለተደራጁ 255 ወጣቶች በእጣ አስተላለፈ። 

የርክክብ ስነ-ስርዓቱ ዛሬ በተከናወነበት ወቅት የክፍለ ከተማው የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መዝገበ ልኡል እንደጠቆሙት፤ በቦሌ አራብሳ ኮንዶሚኒየም ሳይት እድሉን ያገኙት ወጣቶች ከክፍለ ከተማው ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡና በማህበር የተደራጁ ናቸው፡፡

መንግስት በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተላለፋቸው እነዚህ የኮንዶሚኒየም ሱቆች ወጣቱን ይበልጥ ተጠቃሚ ሊያደርጉ በሚችሉ የስራ መስኮች እንዲሰማራ እድል የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በሚሊዮኖች በሚቆጠር ገቢ ለባለሀብቶች በጨረታ ይተላለፉ የነበሩትን እነዚህን ሱቆች መንግስት ሲያስተላልፍ የወጣቱን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ በማለም እንደሆነ ገልጸዋል።

በሱቆቹ የሚጠቀሙት ወጣቶች በመረጡትና ያዋጣናል በሚሉት መስክ እንዲሰማሩ በቂ ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

ክፍለ ከተማው በበጀት ዓመቱ 40 ሺህ ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ 37 ሺህ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጸው፤ በቀጣይም ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሰራ አብራርተዋል።

ለማህበራቱ ተወካዮች የሱቆቹን ቁልፍ ያስረከቡት የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ፈቃዱ እንደጠቀሱት፤ ከሱቆቹ መንግስት በርካታ ሚሊዮን ብር ያገኝባቸው ነበር።

ነገር ግን ለወጣቱ ጥያቄ መንግስት ቅድሚያ በመስጠት በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች ሱቆቹን ማስተላለፉን ገልጸዋል።

ወጣቶቹ ባገኙት እድል ተጠቅመው ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ሌሎች ወጣቶችን በመቅጠር ለስራ እድል ፈጠራው የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈሚው ''ወጣቱን ወደብልፅግናው ማምጣት የመንግስት ዋና ተግባር ነው'' ብለዋል።

የእድሉ ተጠቃሚ ከሆኑት ወጣቶች መካከል ወጣት ሀዊ ሂቦ እና ወርቁ ፍቃዱ በበኩላቸው ያገኙትን እድል በመጠቀም ራሳቸውንና ወገናቸውን ለመጥቀም በትጋት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ውጤታማ በመሆን ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚጥሩም ጠቁመዋል፡፡

ሱቆቹን ለማስተላለፍ የነበረው ሂደት ግልጽነት የተሞላው እንደነበረም አረጋግጠው፤ ''መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንዲህ አይነት ግልጽነት ያለው ተግባር ማከናወን ይገባል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም