ቫይረሱን ለመከላከል ህብረተሰቡ የጤና ባለሙያዎች ጥረት እንዲያግዝ ተጠቀ

65

መቀሌ ግንቦት 25 /2012( ኢዜአ) በትግራይ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የጤና ባለሙያዎች እያደረጉ ያሉት ጥረት ህብረተሰቡ እንዲያግዝ ተጠየቀ። 

የክልሉ ኮሮና መከላከል ቴክኒክ ኮሚቴ ንኡስ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ  ዶክተር  ሓጎስ ገዲፋይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የጤና ባለሙያዎች እያደረጉት ያለውን ጥረት የሚያስመሰግን  መሆኑን ተናግረዋል።

“ጥረታቸው በማህበረሰቡ ንቁ ተሳትፎ ካልደገፈ   የስራ ትጋት  ብቻ  ኮሮናን መከላከል አይቻልም “ብለዋል።

ቫይረሱን ለመከላከል አብዛኛዎቹ የጤና ባለሙያዎች በማቆያ ፣ ምርመራና ህክምና ማዕላት ጊዜያቸው እያሳለፉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለሙያቸው  ተሰልፈው  በስራ ጫና ምክንያት እስከ ሁለት ወራት ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ሳይገናኙ የቆዩ  የጤና ባለሙያዎች እንዳሉ ዶክተር  ሓጎስ ገልጸዋል።

ጥረቱ  ዋጋ የሚኖረውም በህብረተሰቡ ተሳትፎ ሲታገዝ  ቢሆንም ከጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉ መልዕክቶች ተግባራዊ አለማድረግና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌዎችን  የመጣስ ሁኔታ እንደሚስተዋል አውስተዋል።

ቫይረሱን ለመከላከል ቤት መቀመጥ አሊያም የግድ ሆኖ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ካስፈለገም  የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል መጠቀምና ርቀትን መጠበቅ  ነው።

ዶክተር  ሓጎስ የጤና ባለሙያዎችና የፀጥታ አካላት በሚያደርጉት  ጥረት ብቻ  ቫይረሱን መከላከል አዳጋች በመሆኑ ህብረተሰቡ  ከራሱ ጀምሮ በመጠንቀቅና  ሌላውንም  በማስተማር ተሳታፊ በመሆን እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

በክልሉ  ናሙና በመውሰድ  ለመመርመር  በላብራቶሪ ዘርፍ ተጨማሪ  700  የጤና ባለሙያዎች አሰልጥነው መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

ግብረ ኃይሉ  ከጎረቤት ሀገራት ድንበር አቋርጠው ወደ ክልሉ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ የማቆያና ምርመራ  ማዕከላት በተጨማሪ ለመቋቋም የጤና ሚኒስቴርን ድጋፍ ጠይቀዋል።

በተለይም በሰቲት ሑመራና አካባቢው ካለው የእርሻ ስራ  እንቅስቃሴ የሚገባው የጉልበት ሰራተኛ ቁጥርም  እየጨመረ በመምጣቱ የወረርሽኙ  ስጋት ማሳደሩንም ጠቁመዋል።