የትምህርት ሚኒስቴር አመራር ና ሠራተኞች ደም ለገሱ

172

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ)  በኮሮና ቫይረስ የሚከሰትን የደም አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ የትምህርት ሚኒስቴር አመራር ና ሠራተኞች ደም ለገሱ፡፡ 

 የሚኒስቴሩ አመራር  ና ሠራተኞች  በኮሮና ቫይረስ የሚከሰትን የደም አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ የቀረበን ጥሪ መሠረት በማድረግ ነው  ደም የለገሱት። 

  ቀደም ሲል የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት   አገራዊ የደም አቅርቦት በመቀነሱ የልገሳ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።

በልገሳ ፕሮግራሙ የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ነቢል ማህዲ የኮሮናቫይረስ ከመግባቱ በፊት ሲቀርብ የነበረው ደም በመቀነሱ በችግር ጊዜ ሕዝብና አገርን የማሻገር ሃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።

የደም ልገሳው እስከ ነገ የሚቀጥል ሲሆን ከመጪው ዓርብ ጀምሮም የኮሮናቫይረስ መከላከል ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችና የ”ማዕድ ማጋራት” መርሃ ግብር ለመሳተፍ መታቀዱን ገልጸዋል።

ይህን የሚያስተባብር ኮሚቴ መዋቀሩንና በክልሎችም በተመሳሳይ እንደሚሰራም አክለዋል።

መምህራንና ተማሪዎች ራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየጠበቁ ደም እንዲለግሱም ጥሪ አቅርበዋል።

የሚኒስቴሩ የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር ትምህርት ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ለገሰ ነጋሽ ዛሬ የለገስነው ደም ነገ ለእኛው ነው ብለዋል።

ስለሆነም  ከቫይረሱ እየተጠበቁ በቀናት የሚተካውን ደም በመለገስ አገር መውደድን በተግባር ማሳየት ይገባል ነው ያሉት።

ብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ነርስ አቂል ከድርም ኮሮናቫይረስ መግባቱን ተከትሎ በአገሪቱ የደም ልገሳ ተቀዛቅዞ እንደነበረ አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ደም ለግሰው በኮቪድ-19 ዘመን ደም ለሚያስፈልጋቸውና የተለያየ የጤና እክል ላለባቸው ወገኖች በመለገስ ሕይወት እንታደግ ሲሉ መልዕክት ካስተላለፉ ወዲህ መሻሻሉን ገልፀዋል።

ትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ደም የመለገስ ፍላጎታቸውን እያሳወቁ እንደሆነም ነርስ አቂል ገልፀዋል።

የአገሪቷን የደም አቅርቦት ችግር ማቃለል የሚችሉ 600 ሺህ መምህራንና 26 ሚሊዮን ተማሪዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።