የሚሊኒየም አዳራሽ ኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ሕሙማንን መቀበል ጀመረ 

142

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ሕሙማንን መቀበል ጀመረ። 

ባለፉት ሁለት ወራት ማዕከሉን የማደራጀት ሥራ ሲሰራ መቆየቱን የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እስማኤል ሸምሰዲን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ማዕከሉ 40 የጽኑ ሕሙማን መኝታዎችና 1 ሺህ ጽኑ ያልሆኑ ሕሙማን ታካሚዎች አገልግሎት መስጠት ይችላል።

ጎን ለጎንም የላቦራቶሪ፣ የመድሃኒት ቤት፣ የጤና ባለሙያዎች ልብስ መቀየሪያ፣ መታጠቢያዎችና ሌሎች ክፍሎችም ተዘጋጅተዋል።

በማዕከሉ ተኝተው ለሚታከሙ ሕሙማንና ለጤና ባለሙያዎች አስፈላጊ ግብዓቶች መሟላታቸውንም ጠቅሰዋል።

በተጓዳኝም ከማዕከሉ የጥበቃ ሠራተኞች ጀምሮ የሕክምና አገልግሎት ለሚሰጡ ነርሶችና ዶክተሮች ሥልጠናም ተሰጥቷል።

በዚህ መሰረት የማዕከሉ ዝግጅት ተጠናቆ ዛሬ ህሙማንን መቀበል መጀመሩን ነው ዶክተር እስማኤል የገለጹት።

በማዕከሉ ሕሙማን አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኙ፤ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ሠራተኞችም ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ትኩረት መሰጠቱንም አክለዋል።

በተለይም የአየር ሥርዓት ፍሰቱን ለማስተካከል የሚረዱ መሣሪያዎች መገጠማቸው ተጋላጭነትን ለመቀነስ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አስረድተዋል።

ከማዕከሉ የሚወገዱ ፍሳሾች ለብቻ እንደሚወገዱና ደረቅ ቆሻሻዎችም በዘመናዊ መሣሪያ በመታገዝ የሚወገዱ መሆኑንም ዶክተር እስማኤል ተናግረዋል።  

በማኅበረሰቡ ዘንድ የኮቪድ-19 ማዕከላትን የመፍራት ሁኔታዎች መኖሩን የጠቆሙት ዶክተር እስማኤል ይህ አመለካከት ሊቀየር እንደሚገባም አሳስበዋል።

በዚህ ረገድ በማዕከሉ ለሕሙማን የጤና ትምህርቶችና የአካል ብቃት እንቅስቃሴም ጭምር ለመሥጠት ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።  

ኅብረተሰቡ የቫይረሱን ስርጭትና ተዛማችነት ከግምት በማስገባት የመከላከል ሥራውን ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

ማዕከሉ እስከ 1 ሺህ 200 ሕሙማንን የማስተናገድ አቅም አለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም