የህዝቦችን እኩልነት ላከበረ ሃገራዊ አንድነት በጋራ እንስራ …የትግራይ ክልል ምክር ቤት

3377

መቀሌ ሰኔ 29/2010 የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦችን እኩልነት ያከበረ ሀገራዊ መግባባትን በማስቀጠል በህዝቦች መካከል ጠንካራ አንድነት እንዲመሰረት የትግራይ ክልል ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን በያዘው አምስተኛ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባኤ በክልላዊና ሀገራዊ ሁኔታ ላይ ተወያይቶ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

ምክር ቤቱ ባለፉት አመታት በሀገሪቱ የተረጋጋ ሰላም የሰፈነበትና አለም የመሰከረለት የምጣኔ ሀብታዊ እድገት እየተመዘገበ መምጣቱን ገልጿል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዜጎች በፈለጉበት ቦታ ተንቀሳቅሰው የመኖር ንብረት የማፍራት ህገ-መንግስታዊ መብቶች አደጋ ላይ እየወደቁ የሃገሪቱን የእድገት ጉዞ የሚገቱ ጉዳዮችም እያጋጠሙ መሆናቸውን ተመልክቷል።

በህገ-መንግስቱ ምላሽ ያገኙ የክልል ወሰኖችን ባለመቀበል የሚከሰቱ ግጭቶችም ለበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋት ምክንያት እየሆኑ መምጣታቸው የአቋም መግለጫው ያመለክታል።

ምክር ቤቱ በክልሉ፣ በሀገራዊና ወቅታዊ ሁኔታ በመወያየት ከውድቀታችን ጠላት እንጂ የኢትዮጵያ ህዝቦች አይጠቀሙም ብሏል።

ወቅታዊ ሁኔታውን መሰረት በማድረግ ባወጣው ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫው የኢፌዴሪ ህገ-መንግስትን የመጠበቅና የማስጠበቅ ግዴታ አለብን ብሏል።

በህገ-መንግስቱ ላይ የሚፈጸም ጥሰት ወደ ባሰ ችግር ሊከት ስለሚችል ሁሉም ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦብ እንዲቆሙም ጥሪ አቅርቧል።

ህገ መንግስቱ ማሻሻያ የሚያስፈልገው ከሆነም ህግ-መንግስታዊ ሒደቱን በጠበቀ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ያመለከተው መግለጫው ህግን ባልተከተለ መንገድ የሚከናወኑ ተግባራትን በጋራ መከላከል እንደሚገባም አስታውቋል።

በኢትዮ-ኤርትራ ሰላም እንዲመጣ ከሁሉም በላይ የትግራይ ህዝብ እንደሚፈልገው በመግልጽም ድርድሩ የክልሉን ህዝብ ባሳተፈ መልኩ ሊከናወን እንደሚገባ አመልክቷል።

በሀገር ውስጥ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን የህግ ልእልና እንዲረጋገጥና እንዲከበር ያላቸውን ሙያዊ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትን ያከበረ ሀገራዊ አንድነትን የመገንባት ራእይያችንን ለማሳካት ሁሉም ብሄሮችና ህዝቦች በጋራ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡