ቢሮው ከፀጥታ ሥጋት ነፃ ለሆነ የእርሻ ኢንቨስትመንት በትኩረት እየሰራ ነው

107

መተማ፣ ግንቦት 24/2012 (ኢዜአ)  በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚከናወነው የእርሻ ኢንቨስትመንት ከፀጥታ ሥጋት ነፃ በሆነ አግባብ እንዲከናወን እየሰራ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ሰላምና የሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሣይ ዳምጤ የተመራ ልዑክ በመተማ ወረዳ የሚገኙ የእርሻ ኢንቨስትመንት ቦታዎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

በጉብኝቱ ወቅት ኃላፊው እንዳሉት ዞኑ የግብርና ምርቶችን በበቂ መጠን በማምረት ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ሀገራት ገበያ ማቅረብ የሚያስችል እምቅ ፀጋ አለው።

በተለይም ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ሰሊጥና መሰል ምርቶች በስፋት የሚመረትበት አካባቢ መሆኑንም ተናግረዋል።

አካባቢው ባለው ፀጋ ልክ መልማት እንዲችልና የተሻለ ምርት እንዲሰበሰብ ለባለሀብቱም ሆነ ለአርሶ አደሩ የግብርና ልማት እንቅስቃሴ ምቹ የሆነ ሰላምና መረጋጋትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በመሆኑም በቅድመ ዝግጅትም ይሁን በልማት ሥራው ወቅት አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት እንዲኖር የፀጥታ መዋቅሩ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ጠንካራ ቅንጅት ፈጥሮ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው ከውጭም ይሁን ከውስጥ ድንገተኛ የፀጥታ ችግር ቢፈጠር እንኳን በፍጥነት መፍታትና መመከት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም አብራርተዋል።

የፀጥታ ዘርፉን በማዘመንም የልማት እንቅስቃሴዎች ምንም ዓይነት እንቅፋት እንዳይገጥማቸው በቅርበት ሆኖ እንዲያግዝ እንደሚደረግም አቶ ሲሣይ አስታውቀዋል።

በቀጣይም በአካባቢው ልማት እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን በመለየት ተጨማሪ የማስተካከያ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ጠቁመዋል።

“በየዓመቱ የእርሻ ሥራ በሚጀመርበት ወቅት ከጎረቤት ሱዳን ጋር የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ይፈጠራል” ያሉት ደግሞ የዞኑ ሰላምና ሕዝብ ደህንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ናቸው።

በተደጋጋሚ እየተስተዋለ ያለው ክስተትም እልባት እንዲያገኝ የሁለቱን ሀገራት የጋራ ሥምምነት መሠረት ያደረገ መፍትሔ መቀመጥ እንዳለበት ጠቁመዋል።

“ባለሀብቱም ሆነ አርሶ አደሩ መሬቱን በሚያለማበት ወቅት ያለምንም የፀጥታ ሥጋት ሙሉ ጊዜውንና ዕውቀቱን በልማቱ እንዲያውልም ጥብቅ የፀጥታ ክትትል እየተደረገ ይገኛል” ብለዋል።

ዞኑ በአቅሙ ልክ በየጊዜው ከሱዳን አጎራባች የዞን አስተዳደሮች ጋር በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ዙሪያ በመመካከር የሚነሱ ችግሮችን እየተፈቱ እንደመጡ አስታውሰው፤ ችግሩ በሁለቱ ሀገራት መካከል ቀጣይ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የልዑካን ቡድኑ በመተማ ወረዳ ደለሎ፣ ፎርገናና ሎሚናት የተባሉ የእርሻ ልማት ቦታዎችንና በአካባቢው ያለውን የሰላምና ፀጥታ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል።

በጉብኝቱ የክልልና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት አመራሮች ተገኝተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም