በኮሮና ምክንያት የምርት እጥረት እንዳያጋጥም የአርሶ አደሩ ጥረት የሚበረታታ መሆኑ ተገለጸ

107

ሐዋሳ፣ ግንቦት 24/2012 (ኢዜአ) በሀገሪቱ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የምርት እጥረት እንዳያጋጥም አርሶ አደሩ እያደረገ ያለው ዝግጅትና ጥረት አበረታች መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።

አመራሮቹ በደቡብ ክልል ስልጤና ጉራጌ ዞኖች እየተካሄደ ያለውን የግብርና ልማት እንቅስቃሴ በመስክ ጎብኝተዋል።

በዚህ ወቅት የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በጋራ በመንቀሳቀስ የሁሉንም ክልሎች የግብርና ልማት ሥራዎች ተመልክተዋል።

በተለይ በመንግሥት አንድም መሬት ፆም ማደር የለበትም ተብሎ የተያዘው አቅጣጫ እውን እንዲሆን  አርሶ አደሩ እያደረገ ያለው ጥረት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል።

በየደረጃው እየተደረገ ያለው የመኸር እርሻ ዝግጅት በዚሁ ከቀጠለ የምርት እጥረት እንዳይከሰትና ችግር እንዳያጋጥም ያስችላል ብለዋል።

በጉብኝታቸው ወቅት በወረርሽኙ ዙሪያ ለኅብረተሰቡ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ያወሱት አቶ ሙሳ አሁን ያለው መዘናጋትና ግዴለሽነት በፍጥነት መታረም እንዳለበትም አሳስበዋል።

በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የአስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃደር በበኩላቸው ወረርሽኙን ተከትሎ ሊደርስ የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም አርሶ አደሩ  እያደረገ ያለው ዝግጅት የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በስልጤና ጉራጌ ዞኖች አርሶ አደሮች አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው የሚያካሂዱት የእርሻ ልማት ተሞክሮ ለሌሎችም አካባቢዎች ሊስፋፋ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተለይ በኮሮና ቫይረስ መከላከል ዙሪያ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው የፖለቲካና የመንግሥት መዋቅር ተቀናጅቶ ርብርብ ማድረጉን  አድንቀዋል።

በኩታ ገጠም የሚከናወኑ ሥራዎች ውጤታማ ቢሆኑም ከገበያ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ለመፍታት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ሀገርና ሕዝብ ለማዳን መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ ዝግጅት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ካሊድ አልዋን ናቸው።

ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት ሳያደረስ በመሻገር ወደ ሚፈለገው የብልፅግና ማማ ለመውጣት የትኩረት ማዕከል ተደርጎ  እየተሰራ ነው።

"ወረርሽኙ በባህሪው በሁሉም መስኮች ቀውስ ሊያስከትል ይችላል" ያሉት አቶ ካሊድ ከዚህ ችግር ለመውጣት አርሶ አደሩ ተገቢውን ዝግጅት እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም