የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት ህዝቡን ለማወክ የሚሰሩ ሃይሎችን መታገል ይገባል - የኦሮሚያ ክልል

97

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 23/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት ህዝቡን ለማወክ የሚሰሩ ሃይሎችን በመለየት መታገል ይገባል ሲል የኦሮሚያ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ጥሪ አቀረበ።

ቢሮው ህገ-ወጥ ሰልፎችን ለመቆጣጠር መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድና ህዝቡም በትግሉ ያገኘውን ለውጥ ለመጠበቅ ከምንጊዜውም በላይ መትጋት እንዳለበት ገልጿል።

የመንግስትን ትዕግስት እንደ ድክመት የሚቆጥሩና የህዝብን ሰላም ለማወክ ዘወትር የሚጥሩ የፖለቲካ ቡድኖች እና መገናኛ ብዙኃንም ከመሰል ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ቢሮው አሳስቧል።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ መስዋዕትነት የተከፈለበትን የለውጥ ሂደት በአገሪቱ የዴሞክራሲ ምህዳር እንዲሰፋና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲደራጁና አካታች ዴሞክራሲና የብዝሃነት አስተዳደር ሥርዓት እንዲተገበር ያስቻለ መሆኑን ገልጿል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ጅብሪል መሀመድ እንዳሉት፤ ለውጡ ፓርቲዎች አመራሮቻቸው የታሰሩት እንዲፈቱና የተሰደዱት ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዲንቀሳቀሱ እድል የፈጠረ ነው።

በተለያዩ ስልቶች ሁከት ለማስነሳት እየሰሩና ትጥቅን እንደ አማራጭ የያዙ የከተማ ሽብርን በመፍጠር ህዝብ ሰላሙን እንዲያጣ እያደረጉ ያሉ የፖለቲካ ቡድኖች መኖራቸውንም አንስተዋል።

እነዚህ አካላት የማህበራዊ እንዲሁም የመደበኛውን መገናኛ ብዙኃን አውታሮችን በመጠቀም ህዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዲያጣና አገሪቱ ወደ ብጥብጥና ሽብር እንድታመራ የሚሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ህገ-ወጥነትና ህጋዊነትን እያምታቱ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ኃይሎች የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ህዝብን በማደናገር ችግር ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸው እንደተደረሰበት ጠቁመዋል።

እነዚህ ሃይሎች በህዝቦች መካከል የብሔር፣ የሃይማኖትና የህዝብ ለህዝብ ግጭት ለመፍጠር እየሰሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

''የእነዚህን የፖለቲካ ቡድኖችና ግለሰቦች ድርጊት ህዝብ ተረድቶ ሊታገላቸው ይገባል'' ብለዋል።

መንግሥት እነዚህን ኃይሎች መቆጣጠር አቅቶት ሳይሆን፣ ዴሞክራሲን ለማስረፅ እየሰራ በመሆኑና ከእነዚህ ድርጅቶች በስተጀርባ ሆነው አስተሳሰባቸውን እየደገፉ ያሉትን መብት ለማክበር ሲል መታገሱን ገልፀዋል።

''ሆኖም መንግሥት ለጥቂቶች ሲል ብዙሃንን አሳልፎ አይሰጥም'' ነው ያሉት አቶ ጅብሪል።

መገናኛ ብዙኃን መሰረታዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማስፈፀሚያ ሆኖ ሳለ በተቃራኒው የሚሰሩ መገናኛ ብዙኃን መስተዋላቸውን ጠቅሰው፤ ''በድርጊታቸው ከቀጠሉ መንግሥት እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል'' ብለዋል።

'የህግ ጥሰት በመፈጸም አገርን አተራምሳለሁ' የሚልን መገናኛ ብዙኃንን መንግሥት እንደማይታገስ ገልጸዋል።

ድብቅ አጀንዳ ባላቸው ሰዎች እየተጠራ ያለ ሰልፍ የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትልና ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ተናግረዋል።

''መንግሥት ህገ-ወጥ ሰልፎችን ለመቆጣጠር እርምጃ ይወስዳል'' ያሉት አቶ ጅብሪል፤ ህዝቡም በትግሉ ያገኘውን ለውጥ ለመጠበቅ ከምንጊዜውም በላይ በትጋትና በኃላፊነት እንዲንቀሳቀስ አስገንዝበዋል።

የፀጥታ አካሉ የህዝብን ሰላም የሚያውኩ ኃይሎችን ለህግ እንዲያቀርብ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ህብረተሰቡ ከጎኑ በመሆን ሚናውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም