የኮሮና ቫይረስን የሚከላከሉ በጤና ባለሙያዎች የተለዩ ምግቦች የሉም

102

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 23/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) እስካሁን  የኮሮና ቫይረስን የሚከላከሉም ሆነ የሚያድኑ በጤና ባለሙያዎች የተለዩ የምግቦች አለመኖራቸውን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ገለጹ።

ኅብረተሰቡ አሁንም በመንግሥትና በጤና ባለሙያዎች የሚቀርቡለትን መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ከቫይረሱ ራሱንና ወገኑን መከላከል እንደሚገባው ጠቁመዋል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ እስካሁን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ከበሽታው ለማዳን 'ይህ ምግብ ይሆናል' የሚል ምንም አይነት የተረጋገጠ ነገር የለም።

ያም ሆኖ ኅብረተሰቡ በማንኛውም ሁኔታ ጤናን ለመጠበቅ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት መከተልና ማዘውተር እንዲሚገባው አስገነዝበዋል።

''ኅብረተሰቡ በሚመገባቸው ምግቦች ሳይዘናጋ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ሳያስተጓጉል አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል'' ብለዋል።

አሁን ላይ የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ሊያ፤ ኅብረተሰቡ እስካሁን የሚያደርጋቸውን የመከላከያ ተግባራት ይበልጥ ሊያጠናክር እንደሚገባ ገልጸዋል።

በኅብረተሰቡ ዘንድ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ አጠቃቀም ላይ መሻሻሎች መታየታቸውን ገልጸው፤ በዚህ ላይ አካላዊ ርቀትን መጠበቅን በማከል ቫይረሱን መከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል።

'አካላዊ ርቀትን መጠበቅና እቤት መቀመጥ' የሚሉትን መመሪያዎች በመተግበር ረገድ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ የሚወጡትን መመሪያዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የግለሰብ ብቻ ሳይሆን የተቋማት ኃላፊነት በመሆኑ በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የበሽታው ስርጭት ይበልጥ እንዳይስፋፋና የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ሁሉም አካል በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ እንዳለበት አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 172 የደረሰ ሲሆን በበሽታው የሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 11 ደርሷል፤ 209 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም