በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎችን ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው

73

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 23/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በህገ ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎችን መቆጣጠር የጸጥታ መዋቅሩ ቁልፍ ተግባሩ አድርጎ እየሰራ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት ገለጸ።

ኢትዮጵያን በሚያጎራብቱ አገሮች ያለው የኮሮናቫይረስ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል።

ይህን ተከትሎም በእነዚህ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት በመመለስ በአዋሳኝ አካባቢዎች በተዘጋጁ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያዎች ክትትል እያደረጉ ነው።

"ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዚህ በተቃራኒ በህገ-ወጥ መንገድ በእግራቸው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዜጎች ተበራክተዋል" የሚል ሃሳብ እየተነሳ ይገኛል።

ኢዜአ በድንበሮች አካባቢ ያለውን አጠቃላይ የቁጥጥር ሰርዓት አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁንን አነጋግሯል።

በህገ ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ  የሚገቡትን ሰዎች  በኬላዎች ላይ ብቻ ለመቆጣጠር  የሀገሪቱ  ስፋት  ስራውን  አዳጋች  ቢደርገውም  ቁጥጥሩን ከመቼውም በላይ በማጥበቅ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እየተሰራ ነው ብለዋል  ኃላፊው፡፡ 

አክለውም ስራው በጸጥታ መዋቅሩ ብቻ ውጤታማ ባለመሆኑ በድንበሮች አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አቶ ንጉሱ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪ የክልሎችን ሁኔታ በየጊዜው በመከታተል አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱንም ነው የተናገሩት።

ኮሚቴው በምስራቁ የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢዎች በታየው የከፋ የዜጎች እንቅስቃሴ ላይ አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ ሁኔታውን ማስተካከል መቻሉንም ለአብነት አንስተዋል።

በአማራ ክልል መተማ አካበቢ መሰል ችግር እየተነሳ መሆኑን ገልጸው፤ ችግሩን ለመፍታት የፌዴራልና የክልል መንግስታት ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በአጎራባች አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው የመመለስ ፍላጎት ካላቸው እንቅስቃሴያቸውን በህጋዊ ኬላዎች የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸውም አቶ ንጉሱ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም