የኮቪድ-19ን መከላከል መርሆዎችን የመተግበርና የማስተግበር ኃላፊነት አለብን

154

 አዲስ አበባ  ግንቦት 23/2012 (ኢዜአ) የዜጎች ጥንቃቄ አሁን ባለበት ሁኔታ ከቀጠለ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት ፍጥነት ሊባባስ እንደሚችል ተገለፀ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የመድረክ ሊቀመንበርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ የኢ.ዜ.ማ ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ኦባንግ ሜቶን ወረርሽኙን አስመልክቶ አነጋግሯል።

ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ የተለያዩ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከ ማወጅ ቢደረስም በኅብረተሰቡ ዘንድ የጥንቃቄ ጉድለቶች እንደሚስተዋሉ ነው የተገለጸው።

በመንግስት በኩል የሚወሰዱ የመከላከል እርምጃዎች ከሞላ ጎደል ጥሩ ቢሆኑም በተለይ የመንግስት ባለስልጣናት መጀመሪያ አካባቢ በመዲናዋ እየተዟዟሩ ሲያደርጉት የነበረው ሕዝቡን የማንቃት እንቅስቃሴ መቀዛቀዙን ጠቅሰዋል።

የእምነት ተቋማትም በመጀመሪያው አካባቢ ከመንግስት ጎን በመቆም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ያደረጉት ጥረት መልካም ቢሆንም አሁን ሁኔታው ወደነበረበት እየተመለሰ ይመስላል ብለዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አቶ ኦባንግ ሜቶ በበኩላቸው ወረርሽኙን መከላከል የሁሉንም የጋራ ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ “ኢትዮጵያዊነታችንን፣ አንድነታችንን እና አብሮነታችንን ማሳየት ያለብን ወቅት ነው “ሲሉ ተናግረዋል።

የኢዜማ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ የፖለቲካና ሌሎች ልዩነቶችን ማራመድ የሚቻለው ህዝብ ሲኖር በመሆኑ  በማህበረሰቡ ላይ የተጋረጠውን የኮሮና  አደጋ መከላከል ላይ ቅድሚያ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይ የቫይረሱ ስርጭት እየሰፋ ሲሄድ የዜጎች ቸልተኝነትም እየጨመረ መምጣቱ ወደባሰ ችግር ውስጥ ሊያስገባ እንደሚችል ነው ያሳሰቡት አስተያየት ሰጪዎቹ።

የቫይረሱን ስርጭት የመከላከልና ሕዝብን የማንቃት ስራው በመንግስት፣ በእምነት ተቋማት፣ በበጎ አድራጎት ማኅበራት፣ በእድሮችና በሌሎችም ሊጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።

ወቅቱ ማናቸውንም ሕዝብን ከሕዝብ የሚለዩ የፖለቲካም ይሁን ሌሎች አጀንዳዎችን ወደጎን በመተው በአንድ ልብ መተባበርን እንደሚጠይቅም አስገንዝበዋል።

ማኅበረሰቡ ኮቪድ-19ን ከመከላከል አኳያ የሚያሳየው ቸልተኝነት ዋጋ ሊያስከፍል በመቻሉ የጤና ባለሙያዎችን ምክር በመስማት የኮሮና ወረርሽኝ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይደርስ ሁሉም  የበኩሉን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ናቸው።  

ቫይረሱ አንዱን ገድሎ ሌላውን የሚተው አይደለም ያሉት ፕሮፌሰሩ የመከላከያ መርሆዎች አተገባበር ላይ ሁላችንም የፀጥታ ኃይል ሆነን ልናስተገብር ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም