የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ ነው - የጤና ሚኒስቴር

176

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 23/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከተለያዩ አካላት እየተደረገ ያለው የገንዘብና የአይነት ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ይህን የገለጸው ክሪስታል አውቶሞቲቭ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት የቫይረሱ ሥርጭት እስኪያበቃ በአዲስ አበባ ለሚገኙ አምቡላንሶች የእጥበትና የኬሚካል ርጭት አገልግሎት እንደሚሰጥ ባስታወቀበት መርሃ ግብር ነው።  

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰሀረላ አብዱላሂ እንደገለጹት፣ የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል የቀረበውን አገራዊ ጥሪ ተከትሎ በርካቶች ድጋፍ እያደረጉ ነው ።

ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት የሚያስመሰግን በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ምስጋናው አረጋም ሁሉም በተሰማራበት ሙያ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከተወጣ በሽታውን መከላከል እንደሚቻል ተናግረዋል።

በተለይ ቫይረሱን ለመከላከል የሚተጉ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎችም ደህንነታቸው ተጠብቆ  ሥራቸውን እንዲሰሩ ማድረግ ዋነኛው መሆኑን በመጥቀስ።

ለኮቪድ-19 ግልጋሎት ለሚውሉ አምቡላንሶች የሚያደርጉት እጥበትና የኬሚካል ርጭት የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በማገዝ አገራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት መሆኑን የክሪስታል አውቶሞቲቭ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ውብሸት ገልጸዋል።

የቫይረሱ ሥርጭት በቁጥጥር ስር እስከሚውል ድረስ ለአምቡላንሶች ቅድሚያ በመስጠት አገልግሎት እንሰጣለን ነው ያሉት።

ወደ ተቋሙ ለአገልግሎት የሚመጡ ተሽከርካሪዎችን ከመኪና እጥበት ባሻገር፣ የኬሚካል ርጭት እያከናወኑ እንደሆነም ተናግረዋል።

ለኬሚካል ርጭት አገልግሎት የሚውል ቁሳቁስ ከአገር ውስጥ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀትና ከውጭ በማስመጣት ጥቅም ላይ እንደሚያውሉም ጠቁመዋል።

ድርጅቱ በቀን ከ100 በላይ ለሚሆኑ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳለውም አቶ ዳዊት ጨምረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም