አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው ሪፖርት ሚዛናዊነት የጎደለውና ተቀባይነት የሌለው ነው... የአማራ ክልል መንግስት

84

ባህርዳር፤ ግንቦት 23/2012(ኢዜአ) አምነስቲ ኢንተርናሽናል በጎንደርና አካባቢው የተፈጠረውን ግጭትና የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ያወጣው ሪፖርት ሚዛናዊነት የጎደለው በመሆኑ እንደማይቀበለው የአማራ ክልል መንግስት አስታወቀ።

ሪፖርቱ የግጭቱን መንስኤ፣ ችግሩን ለመፍታት የተሄደበትን ርቀትና የመጣውን ውጤት የማያሳይ፤ የአንድን ወገን ፍላጎት መሰረት ያደረገ በመሆኑ ሚዛናዊነት የጎደለውና አድሎአዊነት የታየበት ነው ተብሏል።

የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የቅማንት የራስ አስተዳደር ጥያቄ በህገ መንግስቱ መሰረት ቀደም ሲል ምላሽ ያገኘ መሆኑ የሚታወቅ ነው ብለዋል ።

ይሁን እንጂ የተወሰኑ ጽንፈኛ የታጠቁ ሃይሎች በህወሓት እየተደገፉ የራሳቸውን ፍላጎት ለመጫን በፈጠሩት ግጭት በቅማንትና በአማራ ህዝቦች ላይ ሞት፣ መፈናቀልና ንብረት መውደም መከሰቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው ሲል መግለጫው ያትታል ።

በጎንደርና አካባቢው መስከረምና ጥቅምት 2012 ዓ.ም ላይ የተከሰተው ግጭት ከማዕከላዊ መንግስቱ በተገፋው የህወሓት ቡድን እየተደገፈ የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ ማደፍረሱን የክልሉ መንግስት በወቅቱ ማሳወቁንም አውስተዋል።

በዚህም ከ57 ሺህ በላይ የቅማንትና የአማራ ዜጎች በመፈናቀላቸው የክልሉ መንግስት ድጋፍ በማሰባሰብና ቤታቸውን በመገንባት ሁለቱንም ህዝቦች ወደ ነበሩበት አካባቢ እንዲመለሱ መደረጉም በመግለጫው ተጠቅሷል ።

የተፈጠረውን ግጭት የክልሉ ጸጥታ ሃይል ከቅማንትና የአማራ ህዝቦች ጋር በመተባበር በመፍታቱ አሁን ላይ በሰላም አብረው እየኖሩ መሆናቸውንም አቶ ግዛቸው ገልጸዋል።

ሪፖርቱ በግጭቱ የቅማንት ማህበረሰብ ላይ ብቻ ጉዳት እንደደረሰ አድርጎ ማቅረቡና የሞቱ፣ የተሰደዱና ንብረታቸው የወደመባቸውን የአማራ ህዝቦችን የረሳ መሆኑ ሚዛናዊናነት የጎደለውና አድሎአዊ መመሆኑ ማሳያ ነውም ብለዋል።

ሪፖርቱ ሲዘጋጅ የአማራ ክልል መንግስት ሃሳብ ያልተካተተበት በመሆኑ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ላይ በማተኮሩ፤ የክልሉና የፌደራል መንግስታት ችግሩን ለመፍታት የሄዱበትን ርቀትና የመጣውን ለውጥ የሚያሳይ ባለመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርቱን ሲያዘጋጅ ከክልሉ ሰላምና ደህንነት ቢሮ መረጃ አሰባስቤያለሁ ቢልም ቢሮው የሰጠውን ማስረጃ ወደ ጎን በመተው በራሱ ፍላጎት ያዘጋጀው መሆኑን ማረጋገጥ ተችላል ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተመሳሳይ ሁኔታ በርካታ የአማራ ዜጎች ከኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉልና ሌሎች ክልሎች መፈናቀላቸው እየታወቀ በሪፖርቱ አለመካተቱ የድርጅቱን አድሎአዊ አሰራርን የሚያሳይ መሆኑንም በመግለጫው ተጠቅሷል ።

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው ሪፖርት መሰረተ ቢስ በመሆኑ እንደገና እንዲያስተካክል ካልሆነ ግን በክልሉ መንግስት ተቀባይነት እንደማይኖረው ዋና ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም