የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የትንባሆ ህጉን በአግባቡ ተፈጻሚ ማድረግ ይገባል

100

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ሰው በተሰበሰበበት አካባቢ ትንባሆ እንዳይጨስ የወጣውን ህግ በአግባቡ ማስፈጸም እንደሚገባ ተገለጸ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ትንባሆ የማይጨስበት ቀን ነገ ታስቦ ይውላል።

በዓለማችን በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሲጋራ ማጨስ ምክንያት በሚከሰቱ የጤና ችግሮች ህይወታቸውን እንደሚያጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ባደጉ አገራት የሲጋራ አጫሾች ቁጥር እየቀነሰ ሲመጣ በአንፃሩ በታዳጊ አገራት በከፍተኛ መጠን በመጨመር ላይ መሆኑንም እንዲሁ።

በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የሲጋራ አጫሾች ቁጥር በታዳጊ አገራት በከፍተኛ መጠን በመጨመር ዜጎች ለከፋ የጤና ጉዳት እየተዳረጉ ነው።

ኢትዮጵያ ትንባሆን በመከላከል በኩል ጠንካራ ህግ ካላቸው አገሮች አንዷ ብትሆንም ህጉን በማስፈጸም ሂደት ክፍተቶች መኖራቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

በተለይ በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመቆጣጠር የትንባሆ ህጉን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ነው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት።

በጤና ልማትና ጸረ ወባ ማህበር የትንባሆ ቁጥጥር ፕሮጀክት አስተባባሪው አቶ መላኩ ጌታቸው እንደሚሉት በኢትዮጵያ ትንባሆ የሚያጨሱ ሰዎች ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ በበለጠ ለከፍተኛ የጤና እክል ይጋለጣሉ።

"መንግስት የዜጎችን ጤንነትና ደህንነት ለመጠበቅ ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ ትንባሆን መከላከል የሚያስችል ህግ ማውጣት አንዱ ነው" ብለዋል።

የትንባሆ አዋጁ ተሻሽሎ ከወጣ አንድ ዓመት ማስቆጠሩንና ባለፉት ስድስት ወራትም ተፈጻሚ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ጊዜ ሰው በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ሲጋራ ማጨስ እየቀነሰ ቢመጣም በቀጣይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ህጉን ተፈጻሚ ማድረግ እንደሚገባ ነው ያስረዱት።

ትንባሆ ለኮቪድ -19 ከፍተኛ ተጋላጭ የሚያደርግ በመሆኑ በተለይ ሲጋራና ሺሻ በመቀባበል የሚጠቀሙ ዜጎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስተማሪ እርምጃዎችን መውሰድ ወሳኝ መሆኑንም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን  የምርት ደህንነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስናቀች ዓለሙ እንዳሉት በአሁን ጊዜ የትንባሆ አዋጁን በመተግበር በኩል አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የተሻለ ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ በንክኪ የሚተላለፍ በመሆኑ ሲጋራንና ሺሻን ተሰብስቦ ማጨስና ማስጨስ ወረርሽኙን ለማባባስ ከፍተኛ ዕድል አለው።

ይህን ለመከላከልም ባለስልጣኑ ከፍትህ አካላት ጋር በመሆን ይህን በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል።

''በተለይ ከወረርሽኙ መከሰት በኋላ ቁጥጥሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል'' ነው ያሉት ወይዘሮ አስናቀች።

ዳይሬክተሯ እንዳሉት ህዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ትንባሆን የሚያጨሱ ወይም የሚያስጨሱ ሰዎች በየደረጃው ከአንድ ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንዲሁም  የእስር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን በየዓመቱ ግንቦት 23 ቀን የሚከበር ሲሆን ዘንድሮም ለ33ኛ ጊዜ “ወጣቶችን ከኢንዱስትሪ ተፅዕኖ በመከላከል፣ ከትምባሆና ኒኮቲን መጠቀም እንጠብቃቸው።” በሚል ሀሳብ ይከበራል።

በኢትዮጵያ ደግሞ “የትምባሆ ምርቶችን ባለመጠቀም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ጉዳት እንከላከል” በሚል ሃሳብ ታስቦ ይውላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም