በሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

113

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) የፊታችን ዓርብ በሚጀመረው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የሀገር አቀፍ አርንጓዴ አሻራ ኮሚቴ አባላት ጥሪ አቀረቡ።

የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ባገናዘበ መልኩ እንዲከናወን የሚያስችል ሥልት መቀየሱም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በዘንድሮው ክረምት አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል ዕቅድ ነድፋ የዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።

የችግኝ ተከላ ሥራውም የፊታችን ዓርብ ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በይፋ ይጀመራል ተብሏል።

ዕቅዱ እውን ይሆን ዘንድ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሚመራ ብሔራዊ የአረንጓዴ አሻራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል።

ኮሚቴው የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ታዋቂ ግለሰቦችን ያካተተ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን እየተከናወነ ያለውን የችግኝ ማፍላት ሥራ ጎብኝቷል።

በአካባቢው የሚገኙ የመስኖ ልማት ሥራዎችም የጉብኝቱ አካል ነበሩ።

የኮሚቴው አባላት በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ካለፈው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ልምድ በመቅሰም በዘንድሮው ዓመት ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጓል።

ሆኖም ችግኝ የመትከሉ ሥራ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።

የእስልምና ሃይማኖት መምህሩ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ችግኞችን መትከልና አካባቢን መንከባከብ ከምንም ዓይነት ፖለቲካዊ አመለካከት ጋር የሚገናኝ ባለመሆኑ ሥራው የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

ችግኝ መትከልና አካባቢን መንከባከብ በእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮም የሚበረታታ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩ ያለውን ሀገራዊ ፋይዳ በመገንዘብ ችግኝ ከመትከል ባሻገር ዜጎች በእንክብካቤ ላይ ዘወትር መሳተፍ እንዳለባቸው አትሌት ደራርቱ ቱሉ ተናግራለች።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው የችግኝ ተከላ-መርሃ ግብሩ የዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ቀን በሚውልበት የፊታችን ግንቦት 28 በይፋ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

ዝናብ ቀደም ብለው በሚያገኙ አካባቢዎች ችግኝ ተከላ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወነው የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ከአምናው የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም ነው የገለጹት።

ዕቅዱ እውን እንዲሆን በተለይ ሚዲያዎችና የማኅበረሰብ መሪዎች በስፋት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ባለፈው ዓመት የችግኝ መትከያ ቦታዎች እጥረት ተከስቶ እንደነበር አስታውሰው፤ ዘንድሮ ግን መሰል ችግር እንደማይኖር በማረጋገጥ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የኮሮናቫይረስ ሥርጭት እንዳይስፋፋ በማሰብ የችግኝ ተከላው በልዩ ጥንቃቄ የሚከወን መሆኑም ታውቋል።

በመሆኑም ዜጎች እንደሚኖሩባቸው የአካባቢ ሁኔታ በቡድን ተደራጅተውና ርቀታቸውን ጠብቀው ተከላውን እንዲያከናውኑ ሥልት መቀየሱን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለመተከል ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል አብዛኛዎቹ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ዓይነቶች ናቸው።

ችግኞችም በዋናነት በየአካባቢው በተደራጁ ወጣቶች የተዘጋጁ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም