ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ

71

ጎንደር፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ለሁለት ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ መስጠቱን አስታወቁ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አሥራት አፀደወይን ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ቦርዱ ለተቋሙ ምሁራን  የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሰጠው በሥራ ልምዳቸው፣ በምርምር ሥራቸውና በማኅበራዊ አገልገሎት ተሳትፏቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ ነው።

በዚህም በርካታ የምርምር ሥራዎችን በዓለም አቀፍ ጆርናል ላሳተሙት ለዶክተር ጋሻው አንዳርጌና ለዶክተር ንብረት ሞገስ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ዛሬ መስጠቱን አስታውቋል።

በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ዶክተር ጋሻው አንዳርጌ በዩንቨርሲቲው በማስተማር፣ በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ላለፉት 26 ዓመታት ያገለገሉ ናቸው።

ዶክተር ጋሻው በጤናው ዘርፍም 70 ያህል የምርምር ሥራዎችን በማከናወን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ በሆኑ ጆርናሎች ለህትመት አብቅተዋል።

በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው የሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና የአካዳሚክ ዳይሬክተርና የትምህርት ክፍል ኃላፊ እንዲሁም የዳባት ምርምር ማዕከል አስተባባሪ በመሆን ማገልገላቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አስረድተዋል።

ሌላኛው የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙት ዶክተር ንብረት ሞገስ በዩኒቨርሲቲው ላለፉት 14 ዓመታት በእንስሳት ሕክምናና ሣይንስ ኮሌጅ በእንስሳት ሐኪምና መምህርነት፣ በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት አገልግለዋል።

አሁን ላይ በኮሌጁ የድህረ ምረቃ አስተባባሪ በመሆን እያገለገሉ መሆኑን ዶክተር አሥራት አመልክተው  በምርምር ዘርፉም 24 የሚሆኑ የምርምር ሥራዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ በሆኑ ጆርናሎች ለሕትመት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

ምሁራኑ በምርምሩ ዘርፍ ያሳተሟቸው  ሥራዎች  በውጭና በውስጥ ምሁራን ተገምግመው ብቁ መሆናቸው ምስክርነት የተሰጣቸው ናቸው ብለዋል።

በዚህም የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ዛሬ ለሁለቱ ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እንዲሰጣቸው ማጽደቁን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

የጎንደር ዩንቨርሲቲ በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ በአሁኑ ወቅት የሙሉ ፕሮፈሰርነት ማዕረግ ያላቸው ምሁራን ቁጥር አሥር ማድረሱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም