በደሃና ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሁለት ሠዎች ህይወት አለፈ

57

ሰቆጣ፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሄረሠብ አስተዳደር በደሃና ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሁለት ሠዎች ህይወት ማለፉን የወረዳው ፖሊስ ፅህፈት ቤት አስታወቀ ።

የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አበጀ አሠፋ ለኢዜአ እንደገለፁት የትራፊክ አደጋው ዛሬ የደረሰው በወረዳው በአምደወርቅ ከተማ 01 ቀበሌ እየተባለ በሚጠራው ቦታ ላይ ነው።

አደጋውን ያስከተለው  ኮድ 3-18493 አማ የሆነ መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት መሆኑን ገልጸዋል።

የአደጋው መንስኤም ሹፌሩ መኪናውን አቁሞ በሄደበት ወቅት እረዳቱ ለማሽከርከር ሲሞክር መቆጣጠር ባለመቻሉ ሁለት የእግረኛ መንገደኞችን ገጭቶ መግደሉን አስረድተዋል።

በዚህም የአንድ ወጣት ወንድ ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ ሌላኛዋ ወጣት ሴት ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት በአምደወርቅ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ ሲደረግላት ቆይቶ ሪፈር ተብላ ወደ ሠቆጣ ስትሄድ መንገድ ላይ ህይወቷ አልፏል።


አደጋውን ያደረሰው እረዳትና ተሽከርካሪውን አሣልፎ የሠጠው ሾፌር በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አሽከርካሪዎች የያዙትን መኪና የማሽከርከር በቂ ልምድ ለሌላቸው አካላት አሳልፈው መስጠት እንደሌለባቸው በዚህ አደጋ ትምህርት ሊወስዱ እንደሚገባ ዋና ኢንስፔክተር አበጀ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም