በኢትዮጵያ የቫይረሱ ስርጭት እየተባባሰ ቢሆንም የማህበረሰቡ ጥንቃቄ ግን እየተቀዛቀዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የቫይረሱ ስርጭት እየተባባሰ ቢሆንም የማህበረሰቡ ጥንቃቄ ግን እየተቀዛቀዘ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚደረገው ጥረት በማህበረሰቡ ዘንድ ይደረግ የነበረው ጥንቃቄ አሁን ላይ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ተናገሩ።
የቫይረሱ መስፋፋት በየእለቱ እየጨመረ ቢሆንም ቀደም ሲል የነበሩ የመከላከል እንቅስቃሴዎችና ጥንቃቄዎች እየተቀዛቀዙ መሆኑ እየተነገረ ነው።
በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ከታወቀበት እለት ጀምሮ ስርጭቱን ለመግታት በመንግስት በኩል በርካታ የመከላከል እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸው ይታወቃል።
ስብሰባዎችን ማስቀረት፣ የመሸታና መዝናኛ ስፍራዎች እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማትና ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ተደርጓል።
ከቤት ውጭ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግም ግዴታ ሆኗል።
መጨባበጥ፣ ርቀትን መጠበቅ፣ ግዴታ ከሆነ ከቤት አለመውጣትና ስራን በቤት ማከናወን፣ ማህበራዊ መስተጋብሮች እንዲቀነሱ ማድረግና የትራንስፖርት አገልግሎትን ማሻሻል ከተወሰዱ የመፍትሄ አማራጮች መካከል ይጠቀሳሉ።
መንግስት ከሚወስዳቸው የመከላከል ርምጃዎች በተጓዳኝ ማህበረሰቡም በተለያዩ አደረጃጀቶችና በጎ ፈቃደኝነት ጭምር ስርጭቱን ለመከላከል ሲያደርጉት የነበረው ጥረት ጅምሩ አበረታች ነበር።
በተለያዩ አካባቢዎች በበጎ ፈቃደኞች የእጅ ማስታጠብ ተግባራት በስፋት ይከናወኑ እንደነበር ይታወቃል።
በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ በከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እንዲሁም በሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ መልእክቶች ሲተላለፉ እንደነበርም ይታወሳል።
አሁን ላይ ግን እነዚህ ሁሉ ተግባራት የወረት ሆነው መቅረታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የኪነ ጥበብ ሰዎች ተናግረዋል።
የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ ባለበት አጋጣሚ የመከላከል ተግባራትንና ጥንቃቄዎችን ማጠናከር ሲገባ መቀዛቀዙ አሳሳቢ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለይም በትራንስፖርትና በገበያ ስፍራዎች ርቀትን በመጠበቅ ረገድ ሊስተካከል የሚገባው መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያዊያን የኑሮ ዘይቤ አብሮነት የበዛበት ቢሆንም ይህ አስቸጋሪ ወቅት እስከሚያልፍ የሚጠበቅብንን ሁሉ በማድረግ ልናልፈው ይገባል ብለዋል።
ይሄ ችግር ዓለም አቀፋዊ ቢሆንም በጥንቃቄና በመተጋገዝ ብሎም በመደማመጥ ማለፍ የሚቻል መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዚህም ማህበረሰቡ ራሱን፣ ቤተሰቡን፣ አካባቢውን ብሎም አገሩን ከዚህ ወረርሽኝ የመጠበቅ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ ወረርሽኙን ለመከላከል በሚያስችሉ ተግባራት ሁሉ ሞያዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
በዓለም ላይ በኮሮናቫይረስ እስካሁን ከ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሲያዙ ከ367 ሺህ 100 በላይ ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።
ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ህዝቦች ደግሞ ከበሽታው ማገገማቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል።
በኢትዮጵያም እስካሁን 968 ሰዎች ቫይረሱ ሲገኝባቸው የ8 ሰዎችም ህይወት አልፏል።