የሲናና ግብርና ምርምር ማእከል ሶስት የተሻሻሉ የቦሎቄ ዝሪያዎች ለቀቀ

3906

ጎባ ግንቦት 2/2010 የሲናና ግብርና ምርምር ማእከል በምርምር ያገኛቸውን ሦስት የተሻሻሉ የቦሎቄ ዝርያዎች መልቀቁን አስታወቀ፡፡

በምርምር ማእከሉ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ታደለ ታደሰ  እንደተናገሩት በምርምር የተገኙት እነዚሁ ዝርያዎች በሽታንና ተባዮችን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ናቸው፡፡

ዝርያዎቹ ዋበሮ፣ ጎቡና ዶዮ የሚል ሲያሜ የተሰጣቸው ተሰጥቷቸዋል፡፡

በምርምር የወጡት ዝርያዎች ከትናንሽ ነጭና ቀይ ቦሎቄ እንዲሁም ከትላልቅ ነጭ ዥንጉርጉር የቦሎቄ ዝርያ ምድብ እንደሚካተቱም ጠቁመዋል፡፡

ዝርያዎቹ በብሔራዊ የዝሪያ አጽዳቂ ኮሚቴ ከተገመገሙ በኋላ ከሚያዝያ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ እውቅና አግኝተው መለቀቃቸውን አሰረድተዋል፡፡

ለስድስት ዓመታት በምርምር ስር የቆዩትና የተለቀቁ እነዚሁ የቦሎቄ ዝርያዎች በሽታንና ተባይን በመቋቋም በሄክታር በአማካይ ከ20 እስከ 22 ኩንታል ምርት ይሰጣሉ፡፡

በሄክታር የሚገኘው ምርት መጠን ከነባር ዝርያዎች እስከ 21 በመቶ ጭማሪ የሚሰጡ ናቸው፡፡

ተመራማሪው እንዳሉት ዝርያዎቹን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምዛሪን በማስገኘት በኩል ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል፡

በተጨማሪም ጥራጥሬዎቹን በሰብል ፈረቃ ውስጥ በማስገባት ተመሳሳይ የሰብል ዘሮችን በማልማት ምክንያት የጉዳቱ መጠኑ እያደገ የመጣውን የዋግ በሽታ ለመቀነሰም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

ዝርያዎች የወይናደጋና ቆላማ ስነ ምህዳር ላለቸው አካባቢዎች ተስማሚ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

ማእከሉ በምግብ እህል ዘርፍ ከለቀቃቸው የምርምር ውጤቶች በተጨማሪ የአሁኖቹን ሳይጨምር 17 የጥራጥሬና የቅባት ሰብሎችን በምርምር በማውጣት ለተጠቃሚው አድርሷል፡፡

ከጎሮ ወረዳ ሞዴል አርሶ አደሮች መካከል አቶ አብዳ ሁሳ በሰጡት አስተያየት በእጃቸው የሚገኘው የቦሎቄ ዝርያ ዝቅተኛ ምርት ከመስጠቱም በላይ በበሽታ ሰለሚጠቃ የልፋታቸውን ያክል ምርት አግኝተው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉት አሁን የምርምር ማእከሉ ያወጣውን ዝርያ  የመነሻ ዘር በመቀበል ለማባዛት ፍላጎት እንዳለቸው ጠቁመዋል፡፡

የሲናና ምርምር ማእከል በ1978 ዓ.ም ከተቋቋመ ወዲህ የአሁኑን ሳይጨምር 62 በምግብ እህልና በእንስሳት መኖ ላይ ያተኮሩ የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚው ማድረሱን ከምርምር ማእከሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡