የሰሜን ሸዋ አርሶ አደሮች በምርት ዘመኑ ግብአት እጅ በእጅ በመግዛት እየተጠቀሙ ነው

48

ፍቼ፣ ግንቦት 22/2ዐ12 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች በተያዘው የምርት ዘመን ግብአት ከብድር ይልቅ እጅ በእጅ በመግዛት እየተጠቀሙ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መሳይ ወርቁ እንደገለጹት  በዞኑ 13 ወረዳዎች ቀደም ሲል ለአርሶ አደሮች  የምርት ማሳደጊያ ግብዓት የሚቀርበው በብድር ነበር።

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ የቀረበለት የምርት ማሳደጊያ ግብአት  እጅ በእጅ ሽያጭ በመውሰድ እየተጠቀመ ነው።

አርሶ አደሮቹ በምርት ዘመኑ ግብዓት እጅ በእጅ ለመግዛት ከሚያስፈልጋቸው 172 ሚሊዮን ብር ውስጥ 155 ሚሊዮን ብር  ገቢ አድርገዋል፡፡

ለማዳበሪያና ምርጥ ዘር ግዢ ገንዘቡን ገቢ በማድረጋቸውም ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ በመሰረታዊ ማህበራትና በዩኒየኖች በኩል ለመኸር እርሻ የሚያስፈልጋቸውን  271ሺህ 378 ኩንታል ማዳበሪያና ምርጥ ዘር  ቀርቦላቸው እየተጠቀሙ መሆናቸውን ኃላፊው አሰታውቀዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ የምርት ማሳደጊያ ግብአት እጅ በእጅ በመግዛት መጠቀም የቻሉት በመስኖ እርሻ፣ እንስሳት እርባታ፣ ሌሎች የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመከተል ገቢያቸውን በማሳደጋቸው እንደሆነ ተመልክቷል።

የጅዳ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጄ ታደሰ በበኩላቸው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለዓመታት በጋራ ባደረጉት ጥረት አርሶ አደሮች ገቢያቸው እያደገ በመምጣቱ ግብዓት ያለ ብድር የመግዛት አቅም እየፈጠሩ ነው ብለዋል፡፡

ከአርሶ አደሮቹ መካከል የጅዳ ወረዳ የወለቃ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዘነበ ሆርዶፋ እንደገለጹት ባለፈው የምርት ዘመን ያመረቱትን የስንዴ ሰብል በመሸጥ ባገኙት 17ሺህ ብር ገቢ ማዳበሪያ ያለ ብድር ከፍለው በመውሰድ እየተጠቀሙ ነው፡፡

የእጅ በእጅ ግዥው  ከዚህ ቀደም ከብድር ተቋማት የግብርና ግብዓቶቹን ብድር ወስደው እስከ ወለድ ይከፍሉ የነበረውን እንዳስቀረላቸውም አመልክተዋል፡፡

ሌላው የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር መርሻ ደብሬ በበኩላቸው በአካባቢው ምርጥ የቢራ ገብስ ዘር በማባዛት የሚያገኙት ገቢ በመጨመሩ ዘንድሮ ያለ ብድር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በመግዛት ለመኸር እርሻ እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኩታ ገጠም የመስኖ እርሻ ገብስና ስንዴ በማምረት ባገኙት ገቢ የምርት ግብአት በመግዛት ከብድርና ወለድ መላቀቃቸውን  የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ኃይሉ መርዳሳ ናቸው።

ዘንድሮም ለአምስት ሄክታር መሬት የሚበቃ ማዳበሪያ  ግዥ እጅ በእጅ በመግዛት እየተጠቀሙ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አርሶ አደሮች ጊዜና ጉልበታቸውን ገቢ በሚያስገኝ ስራ ላይ በማዋል ከብድርና ወለድ ከመላቀቅ በተጨማሪ ኑሮቸውን ለማሻሻል እንደሚረዳቸውም ገልጸዋል፡፡

በሰሜን ሸዋ በዘንድሮ የመኸር ወቅት 564ሺ ሄክታር መሬት በልዩ ልዩ ሰብል ለማልማት ታቅዷል።

በዚህም 177 ሺህ አርሶ አደሮች የምርት ማሳደጊያ ግብአትና የተሻሻለ አሰራር  ተጠቅመው  እንዲያለሙ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ገልጿል።

ባለፈው የምርት ዘመን ተገኝቶ የነበረው ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ዘንድሮ በእጥፍ  ለማሳደግ ከምርት ግብዓት በተጓዳኝ የተሻሻሉ የግብርና መሣሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች  አርሶ አደሮች ተግባራዊ እንዲያደርጉ በባለሙያዎች እንደሚታገዙም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም