ሚኒስቴሩ በሶማሌ ክልል ለይቶ ማቆያ ለሚገኙና በጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ አደረገ

61

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል ለይቶ ማቆያ ለሚገኙ እንዲሁም በጎርፍ አደጋ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ አደረገ።

ኮቪድ-19 በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና በጊዜያዊነት መፍታት የሚያስችል የምግብና ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል።

የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ ድጋፉ የተደረገው በክልሉ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በለይቶ ማቆያ ለሚገኙና በጎርፍ አደጋ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ነው።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ እንዳሉት ድጋፉ ዜጎችን በጊዜያዊነት ለመርዳታ ያለመ ነው።

በመሆኑም 10 ነጥብ 5 ኩንታል ሽምብራ፤ 1 ነጥብ 75 ኩንታል ምስር፤ 9 ነጥብ 75 ኩንታል ቦሎቄ፤ 21 ነጥብ 2 ኩንታል ሩዝ፤  4 ነጥብ 1 ኩንታል የታሸገ መኮሮኒ፤ 6 ኩንታል ፓስታ፤ እንዲሁም 40 ደርዘን የህፃናት ንፅህና መጠበቂያና 20 ሊትር ሳኒታይዘር ድጋፍ መደረጉ ተገልጿል።

በስፍራው በመገኘት ድጋፉን ያስረከቡት ወይዘሮ አለሚቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት እለት ጀምሮ ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች የሃብት ማሰባሰብ ስራ ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቋቋም መስሪያ ቤቱ የጀመረው እንቅስቃሴ ቀጣይነት ይኖረዋልም ብለዋል።


ድጋፉን የተረከቡት የሱማሌ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰይነብ ሃጂ አደን ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


በሚኒስቴሩ የተበረከተው ድጋፍ በሸበሌ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ለሚኖሩና በጎርፉ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች እንዲደርስ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም