የአሜሪካንና የዓለም ጤና ድርጅት ግንኙነትን እናቋርጣለን---ትራምፕ

62

ግንቦት 22/2012( ኢዜአ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት እንደሚያቋርጡ አስታወቁ።

ትራምፕ ከባለፈው ወር ጀምሮ የዓለም ጤና ድርጅትን ሲወቅሱ የነበሩ ሲሆን ድርጅቱ “መሠረታዊ ኃላፊነቱን” አልተወጣም ብለው፤ የአሜሪካን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያቋርጡ ሲዝቱም ተደምጠዋል።

በዋይት ሃውስ በሰጡት መግለጫ “ዛሬ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ያለንን ግንኙነት እናቋርጣለን።

እናደርግ የነበረውን ድጋፍ ወደሌሎች ዓለም አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና በጎ አድራጊዎች እናዘዋውራለን” ብለዋል።

አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ አገሮች ግንባር ቀደሚ ናት ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

ባለፈው ዓመት እንኳን ከ4 መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ደጉማለች።

ዳግመኛ ለመመረጥ ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉት ትራምፕ በአሜሪካ የወረርሽኙን ሥርጭት ለመቆጣጠር ተገቢውን እርምጃ አልወሰዱም ተብለው ይተቻሉ።

ድርጅቱ ቻይናን ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተጠያቂ ማድረግ ሳይችል ቀርቷል ሲሉም ወንጅለዋል።

ቻይናን ለመቅጣት የሚወስዷቸውን እርምጃዎች ይፋ ሲያደርጉ “ቻይና የዓለም ጤና ድርጅትን ሙሉ በመሉ ትቆጣጠረዋለች” ብለዋል።

እሳቸው ደግሞ ቻይና በሽታውን ለመደበቅ ሞክራለች ሲሉ ይከሳሉ።

በአሜሪካ ከ 102,000 በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ቁጥሩም ከመላው ዓለም በከፍተኛ ደረጃ የተመዘገበ ነው።

ቻይና የ100 ሺህ አሜሪካውያንን ሕይወት የቀጠፈ ወረርሽኝ ቀስቅሳለች” ያሉት ትራምፕ፤ የዓለም ጤና ድርጅት “ዓለምን እንዲያሳስት” ቻይና ጫና እንዳሳደረችም ተናግረዋል።

ለድርጅቱ ዋና ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም በጻፉት ደብዳቤ “የእርስዎና የድርጅትዎ የተሳሳቱ ውሳኔዎች ዓለምን በእጅጉ ዋጋ እያስፈሉ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

በዚህ ወር መባቻ ላይ የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዛሆ ሊጃን፤ ዶናልድ ትራምፕ ሕዝቡን ለማሳሳት እየሞከሩ ነው ብለው ነበር።

“ቻይናን በመኮነን የአሜሪካን ደካማ ምላሽ ለመሸፋፈን እየሞከሩ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት አባል አገራት በበኩላቸው ለወረርሽኙ የተሰጠውን ዓለም አቀፋዊ ምላሽ የሚያጣራ ገለልተኛ ቡድን ለማዋቀር መስማማታቸውን ዘገባው አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም