መንግስት የኮሮና ቫይረስን በመከላከል የዜጎችን ህይወት የመታደግ ጥረት ያጠናክራል

95

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21/2012  ዓ.ም (ኢዜአ) መንግስት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እና የዜጎችን ህይወት ለመታደግ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ጉድለቶችን በማረም ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተገኙበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የአስፈፃሚ አካል ውይይት ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተካሂዷል።

በውይይቱ መክፈቻ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት፤ ቦርዱ ከተቋቋመ ከአንድ ወር በላይ ያስቆጠረ መሆኑን በመግለጽ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ለአብነትም አዋጁን በማስከበር ሂደት ያሉ ስራዎችን በክልሎች ተዘዋውሮ የመስክ ምልከታ ማድረጉን በመግለጽ ቦርዱ በገለልተኝነት እና በነፃነት እየሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈፀም የወጣው ደንብ እና አፈፃፀም ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ስለ ወረርሽኙ ስርጭትና አሳሳቢነት ኮሚሽኑ የሚገነዘበው መሆኑን በማንሳት መንግስት እየሰራ ያለውን ስራ እንደሚገነዘቡት እና እንደሚያደንቁት ተናግረዋል።

ደንቡን በማስፈፀም ረገድ በአዎንታዊ መልኩ የሚታዩ ነገሮች ቢኖሩም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይኖር ተጣጥሞ ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።

ጠቅላይ አቃ ቤ ህግ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ ወረርሽኙ ለአገሪቱ በአይነቱ ልዩ የሆነ ፈተና በመሆኑ ለከፋ ቀውስ ሳይዳረግ እና ዜጎችን ለመታደግ በሚያስችል መልኩ ምላሽ የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም የወረሽኙን ስርጭት ለመግታት እና ለመከላከል በመደበኛ ህጎች ማስከበር የማይቻለውን የህግ ማስከበር ስራ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምላሽ መስጠት አስፈልጓል ብለዋል።

አዋጁ ከበሽታው ባህሪ ጋር ተዛምዶ የወጣ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ አቃ ቤ ህጓ የህጉ ማዕቀፍ አብዛኛውን መከላከል እና ጥንቃቄ ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ነው ያብራሩት።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አባል ዶክተር ብሩክ ላምቢሶ ደግሞ ለቦርዱ ከቀረቡ አስተያየቶች 80 በመቶ የሚሆኑት አዋጁን በማስፈፀም ረገድ ቸል ተብለዋል፤ እናም ከማስተማሩ ጎን ለጎን እርምጃ ያስፈልጋል የሚሉ ናቸው ብለዋል።

ከመብት ጥሰት ጋር በተያያዘ የቀረበ ነገር አለመኖሩን ተናግረው የዜጎችን ህይወት ለመታደግ እና ትውልድ ለማስቀጠል ከማስተማሩ ጎን ለጎን አዋጁን በትክክል ማስፈፀም የግድ ይላል ነው ያሉት።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የእነዚህ ሁሉ አካላት ሚና እና አላማ ወረርሽኙን በመከላከል እና በመቆጣጠር ዜጎችን ጠብቆ አገር ለማሻገር መሆኑን ጠቅሰዋል።

አለምን ክፉኛ እየፈተነና ህዝብን እያረገፈ ያለው ወረርሽኝ ባህሪው ተለዋዋጭ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶ ትውልድና አገርን ለመታደግ እስካሁን የተሰራው ስራ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ወረሽኙ እንደተከሰተ ግራና ቀኝን ተመልክቶ ህገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የተከተለው አካሄድ ውጤታማ ነው ሲሉም አስምረውበታል።

መንግስት ሁሉንም አቅም ተጠቅሞ የግንዛቤ ስራ ለመስራት ብዙ ርቀት መሄዱን እና ለወረርሽኙ ተገቢነት ያለው ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረጉን ገልፀዋል።

በዚህም መንግስት እስካሁን በተባበረ እንቅስቃሴ የዜጎችን ህይወት ለመታደግ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ጉድለቶችን በማረም ጠንካራ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለፁት።