የሊጉ ስራ አስፈጻሚ የውህደት ፕሮግራምና ህገ ደንቡ ወደ ስራ እንዲገባ ወሰነ

273

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21/2012  ዓ.ም ( ኢዜአ) የብልጽግና ሴቶች ሊግ ስራ አስፈጻሚ የውህደት ፕሮግራምና ህገ ደንቡ ለቀጣዩ የሊጉ ምክር ቤት ቀርቦ ወደ ስራ እንዲገባ መወሰኑን አስታወቀ።

ቀደም ሲል በብሔራዊ እና በአጋር ድርጅቶች ስር ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ የቆየው የብልጽግና ሴቶች ሊግ መዋሃዱ ይታወቃል።

ስራ አስፈጻሚው የውህደት ፕሮግራም፣ ህገ ደንብና የአሰራርና አደረጃጀት መመሪያው ለሚቀጥለው ምክር ቤት ቀርቦ ወደ ስራ እንዲገባ ማስተላለፉን የሊጉ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት የተካሄደው የሊጉ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ የውህደቱን ሂደቶችና ያለፉትን ወራት የስራ አፈጻጻም በመገምገምና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ተጠናቋል።

ሊጉ ሴቶችን የማብቃትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን ሲከውን መቆየቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስና ቫይረሱን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎች በሊጉ እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም ሴቶች በኮሮና ቫይረስ እንዳይጎዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የመለየት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው ፤ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።

ሊጉ ሴቶች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን እየከወነ ይገኛል ብለዋል ወይዘሮ መሰረት።