ከ1 ሺህ 600 በላይ ተጨማሪ የገበያ ስፍራዎች ተቋቁሟል .. የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

200

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2012(ኢዜአ) በገበያ ቦታዎች ላይ መጨናነቅ እንዳይኖር ከ1 ሺህ 600 በላይ ተጨማሪ የገበያ ስፍራ እንዲቋቋም መደረጉን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስር የወጣውን የንግድ መመሪያ በሚተላለፉ አካላት  ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አስጠንቅቋል። 


የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በገበያ ማረጋጋት ግብረሃይል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስር የንግድ መመሪያ መውጣቱንና ይህን ተፈጻሚ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ነው።

ከተግባራቱ መካከል በግብይት ስፍራዎች መጨናነቅ እንዳይፈጠር የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገኝበትም ገልጸዋል።

በገበያ ቦታዎች ያለውን መጨናነቅና መተፋፈግ ለመቀነስ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ1 ሺህ 600 በላይ ተጨማሪ ክፍት የገበያ ስፍራዎች እንዲቋቋሙ መደረጉን ተናግረዋል።

”አብዛኞቹ የገበያ ስፍራዎች በቂ የግብይት ስፍራ በሌሏቸው አካባቢዎች ነው”ያሉት ሚኒስትሩ፤ተጨማሪ የግብይት ስፍራዎቹ በግብይት ወቅት የሚታየውን የመጨናነቅ ሁኔታ መፍታታቸውንም አመልክተዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስር በወጣው የንግድ መመሪያ ቁጥር 3/2012 መሰረት ሰዎች ወደ ግብይት ቦታዎች በሚሄዱበት ወቅት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግ እንዳለባቸውና ሲገበያዩም የሁለት አዋቂ እርምጃ ርቀት መጠበቅ እንዳለባቸው ያስቀምጣል።

ከትንሽ እስከ ትልቅ የገበያ መደብሮች (ሱፐር ማርኬቶች) ያሉ ሰራተኞች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክና ጓንት እንዲያደርጉ መመሪያው ያስገድዳል።

የንግድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ለተጠቃሚዎች ውሃና ሳሙና የእጅ ማጽጃ ኬሚካል (ሳኒታይዘር) ማዘጋጀት እንደሚገባቸውም ይገልጻል።

 በንግድ መመሪያው ዙሪያ እየተከናወነ ያለው ስራ የግንዛቤ ማስጨበጥና የገበያ ስፍራዎችን ማቋቋም መሆኑን የገለጹት አቶ መላኩ፤በቀጣይ መመሪያውን በሚተላለፉ አካላት ላይ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል።

ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በንግድና ገበያ ላይ ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ ከፌዴራል እስከ ክልሎች ግብረ ሃይል በማቋቋም የተለያዩ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት በምርቶች ላይ አግባብ ያልሆነ ጭማሪ ባደረጉ ከ36 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ ከቀላል ማስጠንቀቂያ እስከ እስራት የሚደርስ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

”ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሲሚንቶ፣ በአገር ውስጥ በሚመረቱ የዘይት ምርቶችና በሽንኩርት ላይ የዋጋ ጭማሪ እየታየ በመሆኑ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል” ብለዋል።

ከዘይት አምራቾች ጋር ውይይት ተደርጎ በዋነኛነት ምርቶቹን ከፋብሪካው ለማንሳት የሚከፈል ክፍያ መጨመሩና የንግድ ሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ ችግሮች ዋጋ እንዲጨምር ማድረጋቸው እንደሆነምገልጸዋል።

ችግሮቹ ተፈትተው ዋጋ ወደ ነበረበት እንዲመለስ የማስተካከያ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ገልጸው፤መንግስት ከውጭ በሚያስገባው የፓልም ዘይት ላይ ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ እንዳልተደረገና ያለውን አቅርቦት የማሻሻል ስራ እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ መላኩ ያስረዱት።

ሽንኩርት ላይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የታየውን የዋጋ መንስኤ ማጣራት መጀመሩንና መንስኤው የምርት ሰንሰለቱ ላይ ያለ ችግር ከሆነ ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ ገልጸው፤ ችግሩ የምርት እጥረት ከሆነ ደግሞ ከጎረቤት አገሮች ሽንኩርት በማምጣት ዋጋውን የማረጋጋት ስራ ይከናወናል ነው ያሉት።

አልፎ አልፎ ተፈጥሯዊ በሆነ ሁኔታ ሽንኩርትን ጨምሮ አንዳንድ ምርቶች ከሌላው ከመደበኛ ዋጋ ከፍ ያለ ዋጋ ሊኖራቸው የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው፤ ”ይሄ ግን ከሚኒስቴሩ ቁጥጥር ውጪ አይደለም” ብለዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የወጪ ንግዱ የጎላ የሚባል ተጽእኖ እንዳልደረሰበትና በአጠቃላይ በበበጀት ዓመቱ 10 ወራት ውስጥ ከታቀደው 82 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

የ10 ወር ጊዜ ውስጥ የተገኘው ከ2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ13 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።

በዓለም ደረጃ አገሮች በከፊል ኢኮኖሚያቸውን እየከፈቱ መሆናቸውን ተከትሎ የሚገኘው ገቢ በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ የታቀደውን የሚጠጋ ይሆናል ተብሎ ታሳቢ እንደሚደረግም አክለዋል።