የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተሰበሰበ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለብሄራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተበረከተ

88

 አዲስ  አበባ  ግንቦት 21/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ  ወረርሽኝን ለመከላከል የተሰበሰበ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለብሄራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተበረከተ፡፡

ህብረተሰቡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረጉ ጥንቃቄዎችን  በማጠናከርና  በዚሁ ሳቢያ ተጎጂ ሊሆኑ የሚችሉ ዜጎችን በመደገፍ በኩል ሚናው እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል፡፡

በሰላም ሚኒስቴር በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የሃብት አሰባሰብ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተሰበሰበውን  የገንዘብ ድጋፍ ተረክበዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም አምባሳደር ምስጋኑ እንደጠቆሙት፤ የወረርሽኙ ስርጭት በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ ህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ የጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ጫና በመተባበር ለመቋቋም ህብረተሰቡ አቅሙ የቻለውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በሀገራችን የተከሰተውን ይህን ወረርሽን ለመከላከል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ  መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደር ምስጋኑ  ተቋማቱና ድርጅቶቹ ላደረጉት ድጋፍ  በኮሚቴው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰራተኞች፣ የካናዳ ኢቫንጀሊካል ቸርችና ዳንጎቴ ሲሚንቶን ጨምሮ ዘጠኝ የሚሆኑ ድርጅቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች ባደረጉት ድጋፍ 15 ሚሊዮን 100 ሺህ 533 ብር ድጋፍ ተደርጓል።

በወቅቱ ዶክተር ፋንታዬ ይማሙ የተባሉ የህክምና ባለሙያ በአዕምሮአዊ ንብረት የተመዘገበ ሁለት የፈጠራ ስራዎቻቸውን ለዚሁ ተግባርና ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እንዲውል አበርክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም