የሚያጨሱ ሰዎች ለኮቪድ-19 ያላቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ ነው

59

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21/2012  ዓ.ም ( ኢዜአ) ሲጋራና ሺሻ የሚያጨሱ ሰዎች ለኮሮና ቫይረስ ያላቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ባለስልጣን ገለጸ።

አጫሽነትን ለማስፋፋት የሚሰሩ አካላትን ለመከላከል ህብረተሰቡ በትጋት እንዲሰራ ተጠይቋል።

የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን በየዓመቱ ግንቦት 23 ቀን የሚከበር ሲሆን ዘንድሮም በዓለም ለ33ኛ ጊዜ “ወጣቶችን ከኢንዱስትሪ ተፅኖ በመከላከል፤ ከትምባሆ እና ኒኮቲን መጠቀም እንጠብቃቸው!” በኢትዮጵያ ደግሞ ለ28ኛ ጊዜ “የትምባሆ ምርቶችን ባለመጠቀም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ጉዳት እንከላከል!” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።

ባለስልጣኑ የዓለም ትንባሆ የማይጨስበትን ቀን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ ''የኮቪድ-19 ቫይረስ በንኪኪ እና ከትንፋሽ ጋር በሚወጣ ጠብታ የሚተላለፍ በመሆኑ ሲጋራና ሺሻ እየተቀባበሉ በሚያጨሱ ሰዎች መካከል በቀላሉ ይተላለፋል'' ብሏል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኬይሬዲን ረዲ ትምባሆ የሚጠቀም ሰው ከማይጠቀም ሰው አንጻር ለከፋ የጤና እክል እንደሚጋለጥ አስገንዝበዋል።

በባህሪው ሁሉንም የሰውነት አካል የሚጎዳው ትንባሆ የኮቪድ-19 በሽታ ሲጨመርበት ለአስከፊ የጤና ጉዳት እንደሚያጋልጥ አመላክተዋል።

ስለሆነም ወጣቱ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ከሚፈጥረው ተጽዕኖ ራሱን በመጠበቅና የትምባሆ ገዳይነትን በመረዳት ከትምባሆና ኒኮቲን ራሱን መከላከል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ትምባሆ የሚጠቀሙ ሰዎች ጎጂነቱን በመረዳትና በተለይ ከወቅታዊው ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ያለውን ተደራራቢ ጉዳት በመገንዘብ እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ወላጆችና ህብረተሰቡም እነዚህ ሰዎች ከሱስ እንዲወጡ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ሰዎች ወደ ትምባሆ ምርት ተጠቃሚነት እንዲገቡ የተለያዩ የማማለያ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ አካላትን እንዲከላከልም ዶክተር ኬይሬዲን ጥሪ አቅርበዋል።

የትምባሆ አምራች፣ አከፋፋይ፣ አብቃይ፣ ሻጭ እና መሰል የትምባሆ ንግድ ውስጥ የሚሳተፉ አካላት ወጣቱ የምርታቸው ተጠቃሚ እንዲሆን ከሚፈጥሩት ተጽዕኖ መጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተለይም ወላጆች፣ ህብረተሰቡና መልካም ዜጋ መፍጠር ዓላማቸው የሆኑ ሁሉ ተግተው እንዲሰሩ መልዕከት አስተላልፈዋል።

በተለያየ መንገድ የትምባሆ ተጠቃሚነትን የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ የጠቆሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ድርጊቱ ወንጀል መሆኑን ገልጸዋል።

''ወጣቱን የትምባሆ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚፈጸሙ ማናቸውም ተግባራት በአገርና ህዝብ ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ከባድ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በትጋት መከላከል ይኖርበታል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም