መደበኛ ባልሆነ የኢኮኖሚ ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶችን ለመደገፍ ልየታ እየተሰራ ነው

63

 አዲስ  አበባ  ግንቦት 21/2012 (ኢዜአ) በኮሮናቫይረስ  ወረርሽኝ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ መደበኛ ባልሆነ የኢኮኖሚ ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶችን ለመደገፍ እየተለየ መሆኑን የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ገለጸ። 

የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ እንደገለጹት፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት መደበኛ ባልሆኑ የስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለኢኮኖሚ ችግር ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

በተለይም በከተሞች አካባቢ በአነስተኛ የንግድ ስራ የተሰማሩ ሴቶች ከስራ ውጭ በመሆናቸው ለከፋ የኢኮኖሚ ችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል።

”እንደ ቡና አፍልቶ መሸጥ ያሉ ትናንሽ ንግዶች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ቆመዋል” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ለችግሩ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ እና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከብሔራዊ ኮሚቴው ጋር በመነጋገር የኢኮኖሚ ጫና ያረፈባቸውን ሴቶች ለመደገፍ ራሱን የቻለ ዕቅድ ተዘጋጅቶ የልየታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ ወይዘሮ ስመኝ ገለጻ፤ ከውጭ አገሮች እየተመለሱ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

ከስደት ተመላሾቹ በለይቶ ማቆያ ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ ሚኒስቴሩ የሚያደርግላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ህጻናትና ሴቶችን በመከታተል ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ በየደረጃው እቅድ በማውጣት የግልና የመንግስት ድርጅቶችን ድጋፍ በመጠየቅና በማሰባሰብ፣ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሴቶች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።