በአርሲ ዞን የልማት ስራዎች ጉብኝት ተካሄደ

145

አዳማ ግንቦት 21/2012( ኢዜአ ) በአርሲ ዞን ሌሙና ቢልቢሉ ወረዳ በመስኖ እየለማ ያለው አትክልትና ፍሬፍሬ ዛሬ በክልሉ መንግስት እና የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተጎበኘ። 
በጎብኝቱ ወቅት በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል የህዝብና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አወሉ አብዲ እንደገለፁት አርሶ አደሩ መሬቱን   በኩታ ገጠም በማሰባሰብ እያካሄደ ያለው የድንችና ሌሎችንም  ሰብሎች ልማት ትልቅ ተሞክሮና ልምድ የሚወሰድበት ነው።

“አርሶ አደሩ በአንድ ሄክታር ከሚለማ  ድንች ሽያጭ ከሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኝ ተገንዝበናል “ያሉት አቶ አወሉ፣ በደጋማ አካባቢዎች ከሶስት ጊዜ በላይ እያለማ መሆኑን መረዳት እንደቻሉ ተናግረዋል።

በቀጣይም በድንች የተሸፈነውን ማሳ ምርቱን በመሰብሰብና በቢራ ገብስ በመሸፈን ዘላቂ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አርሶ አደሩ ልማቱን ሲካሄድ እራሱን  ከኮሮና በሽታ መጠበቅ ሊሆን እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አርሶ አደር ንጉሴ አባቦ   በሌሙና ቢልቢሉ ወረዳ በሌሙ ቡርቃ አካባቢ  በኩታ ገጠም ማህበር በመደረጃት ድንችን በመሰኖ እያለሙ መሆኑን ጠቅስው  በሄክታር ከሚያለሙት ምርት ሽያጭ  200ሺህ ብር እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

ሆኖም  ቀደም ሲል እስከ 2ሺህ 400 ብር  ይሸጥ የነበረው  አንድ ኩንታል ድንች አሁን ላይ ደላሎች ጣልቃ በመግባታቸው ዋጋው ወደ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር  ወርዶ እየተሸጠ ነው ብለዋል፡፡

“ለልፋታችን ተገቢውን ዋጋ እንድናገኝ የገበያ ትስስር ሊፈጠርልን ይገባል “ብለዋል።

የአርሲ ዞን ግብርና ጽህፊት ቤት ኃላፊ አቶ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው አትክልትና ፍሬፍሬ ሰብል ከ77ሺህ ሄክታር በላይ በመስኖ እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ የገበያ ችግር እንዳይገጥመው ከአጎራባች ክልሎችና አዲስ አበባ አስተዳደር ጋር ለማስተሳሰር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አሰረድተዋል።