የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ወደ ጉጂ ዞን በሚያስገቡና በሚያስወጡ አራት አቅጣጫዎች ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው

61

ነገሌ፣ ግንቦት 21/2012 ( ኢዜአ )በጉጂ ዞን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በጥናት በተለዩ 4 መግቢያና መውጫዎች ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ የዞኑ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ገለጸ፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የግብረ ሀይሉ ሰብሳቢ አቶ ታደለ ኡዶ እንዳሉት ዞኑ ከሀገር ውስጥ ከሱማሌና ከደቡብ ክልል በወሰን  ከውጭ ደግሞ ከኬንያና ከሶማሌ ጋር በድንበር ይገናኛል ፡፡

የኮሮና ቫይረስ በባህሪው ከስፍራ ወደ ስፍራ በሚደረግ የሰዎች ዝውውርና እንቅስቃሴ በአካል ንክኪ የሚተላለፍ ወቅታዊ የጤና ስጋት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የዞኑ መውጫና መግቢያ በሮች በተሽከርካሪ የሚደረግ ህገ ወጥ ንግድና የሰዎች እንቅስቃሴ ዋነኛ የቫይረሱ ማስፋፊያ መንገዶች ሊሆኑ እንደሚችሉ በጥናት መለየቱን ገልፀዋል ።

ለኮንትሮባንድ ንግድና ለሌላም ስራ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእግርና በትራንስፖርት ወደ ጉጂ ዞን የሚገባ የህዝብ ቁጥር የመጨመር አዝማሚያ እንደሚታይበትም ተናግረዋል ።

ይህንኑ ተከትሎ ከአዋሳኝ ክልሎችና ከጎረቤት ሀገራት ወደ ዞኑ በሚገቡ ሰዎች ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል ።

በዞኑ አራት አቅጣጫዎች የሙቀት መለኪያ መሳሪያ፣ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ አንድ ሆስፒታልና 34 የለይቶ ማቆያ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል፡፡

ወደ ዞኑ የሚመጡ ሰዎች የሰውነት ሙቀት ሳይለኩና ምልክት የታየባቸው ደግሞ ወደ ለይቶ ማቆያ ሳይገቡ እንዳያልፉ ለመቆጣጠር በቂ የጸጥታ ሀይል ተመድቧል ፡፡

የአሰራር ክፍተት እንዳይፈጠር ዞኑ ከወረዳ፣ ከቀበሌና ከክልል ግብረ ሀይሎች ጋር በመሆን የእለት ተእለት ስራውን እንደሚገመግምም ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል ።

በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የግብረ ሀይሉ አባልና የአካባቢ ሰላም ማስከበር ሀላፊ ዋና ሳጂን ጉተማ ሳፋዬ በበኩላቸው ፖሊስ ቫይረሱን ለመከላከል የወጡ እገዳዎችንና ክልከላዎችን በማስተግበር ላይ ነው ብለዋል፡፡

የቫይረሱ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱ በመንግስትና በጤና ባለሙያዎች ቢገለጽም በህዝብ ዘንድ መዘናጋት እንደሚስተዋል  ጠቁመዋል፡፡

ፖሊስ ቫይረሱን ለመከላከል ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ሰዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ የተጠያቂነት አሰራር ዘርግቶ አባላቱን አሰማርቷል ።

 በህገ ወጥ ንግድና በኮንትሮባንድ ሰበብ በአሳቻ መንገድና በጫካ ተደብቀው በሚገቡ ሰዎች ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር የተጠናከረ መሆኑንም ዋና ሳጅኑ ተናግረዋል ።

ባለፈው ሳምንት ብቻ ቫይረሱን ለመከላከል የወጣውን ህግና ደንብ የተላለፉ 161 ግለሰቦችና አሽከርካሪዎች ለህግ ቀርበው በገንዘብ መቀጣታቸውን አስታውሰዋል፡፡

የነገሌ ከተማ ነዋሪ አቶ አለማየሁ አሰፋ በሰጡት አስተያየት የግብረ ኃይሉ ክትትልና ቁጥጥር በመደገፍ የበኩሌን ድርሻ አበረክታለሁ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም