የጣና ሃይቅ እምቦጭን ለማስወገድ ተገቢው ድጋፍ እየተደረገ አይደለም

101

ባህር ዳር፣  ግንቦት 21/2012 ( ኢዜአ) በጣና ሃይቅ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ የሚደረገው ድጋፍ አናሳ መሆኑን የጣና ሃይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ ገለፁ።

የኤጀንሲው ስራ አስኪያጅ ዶክተር አያሌው ወልዴ በክልሉ የ9 ወራት እቅድ ግምገማ መድረክ ላይ እንደገለፁት እምቦጭን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ውጤት ማምጣት አልተቻለም ።

በዚህ ዓመት እምቦጩ 4 ሺህ ሄክታር የሃይቁ አካል መውረሩን ገልጸው፤ የህብረተሰቡን ጉልበትና ማሽን በመጠቀም ከ3 ሺህ ሄክታር በላይ ማስወገድ ተችሏል ።

ነገር ግን አሁንም ከአንድ ሺህ ሄክታር የሚበልጠው የሃይቁ አካል በአረሙ እንደተወረረ ነው ብለዋል ።

ፀዳ የተባለውም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ነፃ ነው ማለት እንዳልሆነ ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል ።

አረሙ በባህሪው በቅጠሉ፣ በግንዱ፣ በስሩና በአበባው ጭምር የሚራባና በአንድ ሳምንት ጊዜ እራሱን መልሶ የመተካት አቅም እንዳለው ገልፀዋል።

የአረሙ የመራባት ፍጥነትና ሃይቁን የመውረር አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተው፤ ይህንኑ መመከት በሚያስችል ሁኔታ እየተሰራ አይደለም ብለዋል።

ጣናን እምቦጭ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አደጋዎችም ተጋርጠውበታል ያሉት ዶክተር አያለው ይህን በመደበኛ እንቅስቃሴ ብቻ መግታት አይቻልም ብለዋል ።

ኤጀንሲው አቅሙን አሟጦ አረሙን ለመከላከል ጥረት እያደረገ ቢሆንም ከክልሉ መንግስት ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት እገዛና ድጋፍ እየተደረገ ባለመሆኑ ስራው አስቸጋሪ እንዳደረገው አመልክተዋል።

ከዘጠኝ ወር በፊት ኤጀንሲው ቢቋቋምም እስከ አሁን የሰራተኛ ቅጥር፣ የተሽከርካሪ አቅርቦትና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች አልተሟሉለትም ብለዋል።

ኤጀንሲው ማቋቋም ብቻውን ግብ አይደለም ያሉት ስራ አስኪያጁ በየደረጃው ያለው አመራር የጣና ጉዳይ ያገባኛል ብሎ ሊያግዝና ሊደግፍ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።

አረሙን ለማስወገድ የገቡ ማሽኖች የሃይቁን ስነ ባህሪ መሰረት ያደረጉ ካለመሆናቸውም በላይ ለብልሽት ሲዳረጉ በመለዋወጫ እቃዎች እጥረት ምክንያት ለረጅም ጊዜ እየቆሙ ተቸግረናል ሲሉ አብራርተዋል።

በመጀመሪያ የክልሉን አቅም አሟጥጦ በመጠቀም እምቦጭን ማስወገድ ካልተቻለ ፌደራልና የውጭ ሃገራት ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል።

ጣና ሃይቅ ውስብስብ ችግር አለበት ያሉት ዶክተር አያሌው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጠንካራ ድጋፍ፣ ክትትልና እገዛ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደረ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው የጣና ሃይቅ የተደቀነበት አደጋ ለመታደግ ሳይንሳዊ አሰራርን መሰረት ያደረገ አንቅስቃሴ ይደረጋል ብለዋል ።

በሃይቁ እንክብካቤ ዙሪያ የሃብት እጥረት፣ የእውቀት ክፍተት፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ሌላም ካለ ተገምግሞ አስፈላጊው ማስተካከያ እንደሚደረግ ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።

የሃይቁ ሁለንተናዊ ደህንነት መጠበቅ አለበት ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ጠንካራ የክትትል ስራም መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል ።

የእምቦጭ አረም ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በሐይቁ ላይ  መከሰቱ ይታወቃል።